በክልሉ የፕላስቲክ ምርትን በአግባቡ በመጠቀም የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የተቀናጀ ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የፕላስቲክ ምርትን በአግባቡ በመጠቀም የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የተቀናጀ ተግባር እየተከናወነ ነው

ባህር ዳር / ደሴ ፤ ግንቦት 28/2017 (ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል የፕላስቲክ ምርትን በአግባቡ በመጠቀም የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና ብዝሃ ህይወትን ለመጠበቅ የተቀናጀ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።
"የፕላስቲክ ብክለት ያብቃ" በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም የአካባቢ ቀን በክልል ደረጃ ዛሬ ተከብሯል።
የክልሉ የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ በልስቲ ፈጠነ በመድረኩ እንደገለጹት፤ በየአካባቢው በዘፈቀደ የሚጣሉ የፕላስቲክ ቆሻሻዎች የአካባቢን ስነ-ምህዳር እየጎዱ ናቸው።
የፕላስቲክ ምርትን የምንጠቀምበት አግባብ የአካባቢ ብክለትን በማስከተሉ ለብዝሃ ህይወት መመናመን መንስኤ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ፕላስቲኮች አካባቢን እንዳይበክሉ ተሰብስበው መልሰው ጥቅም ላይ የሚውሉበትን አቅም ይበልጥ ለማጠናከር ከአጋር አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ችግሩን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ከሚከናወነው የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች ባለፈ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመረሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል በባህርዳር ከተማ የሚገኘው አይቸው፣ ሜሮንና ጓደኞቹ የሀይላንድ መልሶ መጠቀም የህብረት ስራ ማህበር ሰብሳቢ አቶ አይቸው ደባስ እንዳለው፤ የወዳደቁ የውሃ መያዣ ፕላስቲኮችን ከሰብሳቢዎች በመረከብ ፈጭተው ለፋብሪካዎች እያስረከቡ ነው።
በተመሳሳይ "የፕላስቲክ ብክለትን እንግታ" በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት በደሴ ከተማ ተካሂዷል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው በወቅቱ እንደገለጹት ፤ ከተማዋን ጽዱ፣ ውብ ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡
የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱን ለማዘመን የፈሳሽና የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ እየተገነባ መሆኑን ጠቁመው ፤ የኮሪደር ልማትም ይህን ለማሳካት አጋዥ መሆኑን አክለዋል።
ሕብረተሰቡ ፕላስቲክ የሚያደርሰውን የአካባቢ ብክለት በመገንዘብ ችግሩን ለመከላከልና ከተማችንን ጽዱና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ሊደግፍ ይገባል ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮናስ ሰይድ ናቸው።
ሁሉም የሚጠቀመውን የፕላስቲክና ሌሎች ቆሻሻዎች በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች በተቀመጡ የቆሻሻ ማስቀመጫ ሥፍራዎች ላይ ሊያስቀምጥ ይገባልም ብለዋል፡፡
ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች ውስጥ አቶ ቢላል መሀመድ በሰጡት አስተያየት ፤ አካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ ከተማችንን ጽዱና ውብ ለማድረግ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡