የትምህርት ጥራትን ማሳደግ የሚያስችል አማራጭ የመምህራን ማሰልጠኛ ማዕቀፍ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን ማሳደግ የሚያስችል አማራጭ የመምህራን ማሰልጠኛ ማዕቀፍ ተዘጋጀ
አዳማ፤ግንቦት 28/2017 (ኢዜአ)፦የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የመምህራንን እጥረት ለማቃለል ያለመ አዲስ አማራጭ የመምህራን ማሰልጠኛ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ከሥርዓተ ትምህርት ለውጥ ጋር ተያይዞ ያዘጋጀውን "የቅድመ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ አማራጭ የመምህራን ማሰልጠኛ ማዕቀፍ" ከሁሉም ክልሎች ለተውጣጡ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ማስተዋወቅ ያለመ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ ወቅት በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት የመምህራንና የትምህርት አመራሮች ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፥ በትምህርት ሥርዓቱ የተማሪዎች ውጤትን ማሳደግና የመምህራን አቅም ማጎልበት ላይ መስራት የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።
ከዚሁ ጎን ለጐን የመምህራን እጥረትን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የመምህራንን ቁጥር ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው ተግባር በተለመደው መንገድ ብቻ በመጓዝ የሚፈለገውን አሃዝ ማምጣት ባለመቻሉ አማራጭ የመምህራን ማሰልጠኛ ማዕቀፍ በሚኒስቴሩ መዘጋጀቱን አውስተዋል።
በመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት ከሚሰለጥኑት መምህራን በተጨማሪ ከተለያዩ የትምህርት መስኮች ወደ መምህርነት ሙያ ለመግባት ፍላጎት ያላቸውን ስልጠና በመስጠት ወደ ሙያው እንዲመጡ ለማመቻቸት እንደሚያስችልም አስረድተዋል።
ማዕቀፉ የመምህራን ሙያን በማጎልበት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እንደሚያስችልም መሪ ሥራ አስፈፃሚው አመልክተዋል።
የሀገር አቀፍ አጠቃላይ የመምህራን ሥልጠና ግብረ ሃይል ሰብሳቢ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሥነ ትምህርትና ቋንቋ ትምህርት ጥናት ኮሌጅ መምህር ካሳ ሚካኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በመደበኛው ትምህርትና ስልጠና የመምህራንን ቁጥር መጨመር አልተቻለም ብለዋል።
በተለይ ንድፈ ሀሳብን ከተግባር ጋር የሚያስተሳስር፣ ስልጠናውን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር ተዛማች የማድረግና ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ መደረጉን አስረድተዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮዽያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አበበ፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች የመምህራን ስልጠና በመቋረጡ ምክንያት እያጋጠመ ያለውን እጥረት ለመቅረፍ ማዕቀፉ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በተለይ የመምህርነት ሙያ ፍላጎትና አቅም ያላቸውን ሰዎች በብዛት ለመሳብና ለማፍራት ወሳኝነት እንዳለውም ገልጸዋል።