የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚመጡ ችግሮችን ለመከላከል የዘርፉ ምሁራን ሚና ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚመጡ ችግሮችን ለመከላከል የዘርፉ ምሁራን ሚና ሊጠናከር ይገባል
ነቀምቴ፤ ግንቦት 29/2017(ኢዜአ)፡- የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚመጡ ችግሮችን ለመከላከል የዘርፉ ምሁራን ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ።
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የመንግስት እና የግል ድርጅት አመራሮች የተሳተፉበት የአለም የአየር ንብረት ቀን በፓናል ውይይት ተከብሯል።
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ዲሪባ ዲባ (ዶ/ር ) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የአየር ንብረት ለውጥ የአለም መንግስታት ትልቅ መነጋገሪያ ነው።
በኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በተለያየ መልኩ እየተከሰተ ጉዳቶችን እያስከተለ መሆኑን ተናግረው መንግስትም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመመከት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የመንግስት ጥረት የበለጠ ውጤት እንዲያመጣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ የዘርፉ ምሁራን ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በተለይም ባላቸው እውቀት እና ልምድ በመታገዝ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመከላከል የሚያግዙ ጥናቶችን በማካሄድ መፍትሄ ጠቋሚ ሀሳቦችን ማፍለቅ መቻል እንዳለባቸውም አክለዋል።
በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በዩኒቨርሲቲው መምህር ቶሌራ መርጋ (ዶ/ር)፤ ''የአየር ንብረት ጉዳይ የሰው ልጅ የመኖር እና ያለመኖር ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት ይሻል'' ብለዋል።
በተለይም የአካባቢ ብክለትን ከሚያባብሱ ችግሮች መካከል የፕላስቲክ ቁሳቁሶችን ያለአግባብ መጠቀም አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የፕላስቲክ ውጤቶች አወጋገድ ስርዓትን በትኩረት መተግበር እንዳለበትም አመልክተዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የአካባቢ ስነ-ምህዳርን ለመጠበቅ የሚደረገው ጥረት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበትም አስረድተዋል።
የነቀምቴ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሀኑ አሰፋ በበኩላቸው ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ምሁራን ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የከተማዋን ፅዳት ለመጠበቅ እና የፕላስቲክ ቁሶችን መልሶ መጠቀም ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረው ለዚሁ ተግባርም ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ህብረተሰቡ የአካባቢ ጥበቃ ስራን ባህል አድርጎ እንዲተገብረው በተከታታይ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የምስራቅ ወለጋ ዞን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ታምሩ ናቸው።
''የተፈጥሮ ሀብትን መንከባከብ እና መተካት እንዲቻል የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው'' ብለዋል።