አረንጓዴ ልማትንና ፅዳትን ከአገር ልማት ጋር አስተሳስሮ ለማስቀጠል መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት የበለጠ ማጠናከር ይኖርባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ልማትንና ፅዳትን ከአገር ልማት ጋር አስተሳስሮ ለማስቀጠል መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት የበለጠ ማጠናከር ይኖርባቸዋል

አዲስ አበባ፤ግንቦት 28/2017(ኢዜአ)፦አረንጓዴ ልማትንና ፅዳትን ከአገር ልማት ጋር አስተሳስሮ በማስቀጠል ሒደት መገናኛ ብዙሀን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት የበለጠ ማጠናከር እንዳለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለፁ።
የሁለተኛው ዙር ፅዱ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ የማስጀመሪያ ስነ ስርዓት አካል የሆነ የፓናል ውይይት እየተካሔደ ይገኛል።
የፓናል ውይይቱ ፅዱ ኢትዮጵያና የአካባቢ ጥበቃን በሚመለከት የመገናኛ ብዙሃን ሚና በሚል የተዘጋጀ ነው።
ውይይቱን አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት፥ ኢትዮጵያውያን አካባቢን ጠብቆ የማቆየት ጥሩ ልምድና ባህል አላቸው።
መንግስት በአረንጓዴ ልማትና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን አስታውቀዋል።
ፅዱ ኢትዮጵያ የዚሁ አካል መሆኑን ገልፀው፤ ንቅናቄው የታለመለትን ግብ እንዲመታ መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
በአገሪቱ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የአካባቢ ጥበቃንና አረንጓዴ ልማትን ታሳቢ አድርገው እየተካሄዱ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በተለይም መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን ፅዱና አረንጓዴ በማድረግ ሒደት ውስጥ ኃላፊነታቸውን ይበልጥ አጠናክረው መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል።
ለዚህም ሁለተኛው ዙር ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ በተለይ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ተከታታይ የሆኑ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
መገናኛ ብዙሃን በጉዳዩ ላይ ከሚሰሩት ስራ በዘለለ ተምሳሌታዊ ተግባራትን በማከናወን የአረንጓዴ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ስራ አካል መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የህዝብና የንግድ መገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡ የስራ ሃላፊዎች በበኩላቸው ጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ መገናኛ ብዙሃን በአገር ግንባታ ላይ ለሚያከናውኑት ተግባር አጋዠ ነው ብለዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በዚሁ ግዜ እንደተናገሩት ባለፉት የለውጥ አመታት መንግስት ዘርፈ ብዙ የልማት ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ተግባራዊ አድርጓል።
በሁሉም መስክ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን ለማስቀጠል ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ የአካባቢ ጥበቃ ስረዓት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት፣ በአካባቢ ጥበቃና መሰል ስራዎች እያከናወነች ያለው ተግባር የላቀ መሆኑን ጠቁመው ይሄንን አጠናክሮ ማስቀጠልና ተደራሽነቱን ማስፋት ይገባል ነው ያሉት።
የአረንጓዴ አሻራና የአከባቢ ጥበቃ ጉዳይ የትውልድ ህልውና ጉዳይ መሆኑንገልጸው በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነታቸውን በተቀናጀ መልኩ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን በአገራዊ ጉዳዮችና በዜጎች ተጠቃሚነት ዙሪያ የጋራ አቋም ኖሯቸው በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ነው ያብራሩት ።
ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የዜጎችን ተሳትፎና ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ የንቅናቄውን ዓላማ እንዲሳካ መገናኛ ብዙሃኑ የሚያደርጉት ጥረት ለአገር ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው፤ ፅዱ ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በህዝቦች አንድነትና ትስስር ዙሪያ ለሚያከናውኑት ተግባር ጉልህ አሰተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት።
በመሆኑም ንቅናቄው ይዞ የመጣውን እድል በአግባቡ በመጠቀም ለአገር ግንባታ ስራው አሻራ ማኖር ይገባል ብለዋል።
የኤን.ቢ.ሲ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብሩክ ከበደ እንዳሉት መገናኛ ብዙሃን አገራዊ ጉዳይን ማስቀጠልና ከዳር ማድረስ ይጠበቅባቸዋል።
ፅዱ ኢትዮጵያ የአንደ ተቋም ብቻ ሳይሆን የሁሉም ተቋማትና ዜጎች የጋራ ጉዳይ መሆኑን ማስገንዘብና ማስረዳት ከመገናኛ ብዙሃኑ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ በሰጡት ማጠቃለያ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ አሻራና ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ መገናኛ ብዙሃን ባከናወኑት ተግባር አበረታች ውጤት ማምጣት ተችሏል።
የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ የዜጎችን ግንዛቤ ማደግን የሚጠይቅ በመሆኑ መገናኛ ብዙሃን በዚህ ረገድ የሚያከናውኑት ተግባር ጉልህ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።
በመሆኑም በሁለተኛው ዙር ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ መገናኛ ብዙሃን የሚያከናውኑትን ተግባር ይበልጥ በማጠናከር ከብክለት የጸዳች ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሒደት ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩም መልእክት አስተላልፈዋል።