የአሰላ ከተማን እድገትና የነዋሪዎቿን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች እየተፋጠኑ ነው

አዳማ፤ ግንቦት 28/2017(ኢዜአ)፦ የአሰላ ከተማን እድገትና የነዋሪዎቿን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች እየተፋጠኑ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።

የአሰላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ስሜ ፀጋዬ ለኢዜአ እንደገለፁት የከተማዋን ነዋሪ የልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በዚህም በከተማዋ የኮሪደር ልማት፣ መናኸሪያ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና የመዝናኛ ማዕከላት ግንባታ እንዲሁም የወንዝ ዳርቻዎችን ፅዱ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማዋን እድገት በማቀላጠፍ ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ ያለመ የመጀመሪያው ዙር 25 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት መገንባቱንም አስረድተዋል።

ከሁለተኛው ዙር የ16 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ ውስጥም የ2 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት ግንባታ በቀጣዩ ወር እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

የአሰላ ከተማን ከሚያቋርጡ አምስቱ ወንዞች በሁለቱ ላይ የወንዝ ዳርቻ ልማት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በከተማ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የዶሮና ወተት ላሞች እርባታ ማዕከላት ተገንብተው መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

በከተማዋ  ለተመዘገበው የልማት ውጤት ባለሃብቶችን ጨምሮ ህብረተሰቡ በሁሉም መስክ እያደረጉ ላለው ተሳትፎ ከንቲባው አመስግነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም