የአካባቢ ብክለትን መከላከልና የአረንጓዴ ልማት ስራን ወጥነት ባለው መልኩ በማከናወን ፅዱ ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2017(ኢዜአ)፦ በመላው ሀገሪቱ የአካባቢ ብክለትን መከላከልና የአረንጓዴ ልማት ስራን ወጥነት ባለው መልኩ በማከናወን ፅዱ ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንደሚገባ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ተናገሩ።

ሁለተኛው ዙር ሀገር አቀፍ ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በአዲስ አበባ በይፋ ተጀምሯል።

በመርሀ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው ብለዋል።

ለዚህም የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው፤ ንቅናቄው ህዝቡ በባለቤትነት የሚሳተፍበትን እድል ያመቻቸ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

የመጀመሪያው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከብክለት የፀዳች ኢትዮጵያን ከመፍጠር በዘለለ ዜጎች በምቹ የኑሮ ሁኔታ የመኖር መብታቸውን ጭምር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ቀደም ሲል በፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

ከዛሬ ጀምሮ በሚከናወነው ሁለተኛው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ወጥነት ያለው የአረንጓዴ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ስራን ማከናወን ይጠበቃል ነው ያሉት።

ለስድስት ወራት በሚቆየው በዚሁ ንቅናቄ ከ15 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የገጽ ለገጽ የፅዳት ዘመቻና መሰል ተግባራትን እንዲያከናውኑ ይሰራል ብለዋል።

በተለይም ለአካባቢ ጥበቃና ብክለትን ለመከላከል አጋዥ እንዲሆኑ ታልመው የወጡ ህጎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በአካባቢ ጥበቃና በብክለት ዙሪያ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በንቅናቄው ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም