በክልሉ ከ278 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ከ145 ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር አገናኝ መንገዶች ግንባታ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከ278 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ከ145 ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር አገናኝ መንገዶች ግንባታ ተከናውኗል
ጋምቤላ፤ ግንቦት 28/2017(ኢዜአ)፦ የጋምቤላ ክልል ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ከ278 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ከ145 ኪሎ ሜትር በላይ ገጠርን ከገጠር የሚያገናኙ መንገዶች የግንባታና ጥገና ስራዎችን ማከናወኑን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር ኡማን ኡጋላ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በገጠር ቀበሌዎች የሚታየውን ገጠር ከገጠር የሚያገናኙ መንገዶች እጥረት ለማቃለል በትኩረት እየተሰራ ነው።
በበጀት ዓመቱ በመንግድ ፈንድ፣ በገጠር ትስስር የምግብ ዋስትና እና በሌሎች ፕሮግራሞች በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች ከ260 ኪሎ ሜትር በላይ ገጠርን ከገጠር የሚያገናኙ መንገዶች የግንባታና የጥገና ስራዎች እያተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በእስካሁኑ ሂደትም ከ145 ኪሎ ሜትር በላይ ከክረምት ከበጋ የሚያገለግሉ የጠጠር መንገዶች ግንባታና የጥገና ስራዎች ተጠናቀው ለትራፊክ ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተጠናቀው ለአገልግሎት ከበቁት መንገዶች መካከል ከአበቦ-ኡኩና-አበሪ መጢ፣ ከአበቦ ፑኬዲ፣ ከኡንጎጊ ኡቴልና ሌሎችም እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
እንዲሁም በግንባታ ሂደት ላይ ከሚገኙት መንገዶች መካከል ደግሞ ከሚጢ ጉማሪ፣ ከተርፋም አኩላና ከካንካን ዲቡክና ሌሎች የገጠር አገናኝ መንገዶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
የመንገዶች መገንባት አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ የግብርና ግብዓትና ምርቱን ለገበያ ለማቅርብና ወላድ እናቶችና ሌሎች ህሙማን ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረላቸው ዋና ዳይሬከተሩ ገልጸዋል።
የመንገድ ግንባታ እየተካሄደባቸው ከሚገኙት ወረዳዎች መካከል የጆር ወረዳ አስተዳዳሪ ኡለም አባላ እንዳሉት በወረዳው በነበረው የመንገድ ችግር ምክንያት ህዝቡ ከቀበሌ ወደ ቀበሌ፣ ከቀበሌ ወደ ወረዳ በእግርና በባህላዊ ጀልባ በውሃ ላይ ሲጓዝ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በወረዳው እየተገነቡ ያሉት መንገዶች ህዝቡ ከነበረበት ችግር ተላቆ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል ብለዋል።
በጆር ወረዳ የኡቴል ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኡኩሪ ኡሞድ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በቀበሌያቸው የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ህዝቡ ሲቸገር መቆየቱን አስታውሰዋል።
ቀደም ሲል በቀበሌያቸው መንገድ ባለመኖሩ ሰው ሲታመም በሸክም ወደ ህክምና ተቋም በመውሰድ ሲቸገሩ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ የዚሁ ወረዳ የኡንጎጊ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኡማን ኡቻን ናቸው።
አሁን ላይ መንገድ ስለተሰራላቸው የታመመ ሰው ወደ ህክምና ለማድረስም ሆነ ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል።