ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን ስኬት አጠናክሮ ለማስቀጠል ለአካባቢ ጥበቃ ተግባር ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን ስኬት አጠናክሮ ለማስቀጠል ለአካባቢ ጥበቃ ተግባር ትኩረት እንደተሰጠ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለፁ።

ሁለተኛው ዙር ፅዱ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ፅዱ ኢትዮጵያ ለከተሞች እድገትና ለዜጎች ምቹ አካባቢን በመፍጠር ረገድ የማይተካ ሚና አበርክቷል።


 

ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን ስኬት ለማስቀጠል የአካባቢ ጥበቃ ተግባር ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግስት ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን በማከናወን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በተከናወኑ ተግባራት ንፅህና ባህል እንዲሆንና ዘመናዊ የአካባቢ ጥበቃ ስረዓት እንዲዳብር ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

ይህም የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቀነስና የጋራ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እድል ፈጥሯል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ፅዱ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄን በማካሔድ ለትውልድ የሚተላለፍ የልማት ስራዎችን ማሳካት መቻሉንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ሁለተኛው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከዛሬ ጀምሮ ለስድስት ወራት የሚቆይ ሲሆን በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል።


 

በመጀመሪያው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የኮሪደርና የወንዝ ዳር ልማት እንዲሁም የፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክቶች፣ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ጨምሮ የመፀዳጃ ቤት ግንባታዎች ተከናውነዋል።

ይህም ንቅናቄው ግቡን እንዲመታ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

በሁለተኛው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄም የሚከናወኑ ተግባራትን ትኩረት ሰጥቶ ማሳካት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

ከብክለት የፀዳች እና ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታ ያሟላች ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አቶ አደም ፋራህ መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ፅዱ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ በአዲስ አበባ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል።

በከተማዋ የፅዱ ኢትዮጵያ አላማን ከግብ ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

በከተማዋ በተለይም በኮሪደር ልማት ከተማዋን የሚመጥን፣ የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽልና አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚጨምር የልማት ስራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የውሀ ብክለትን መከላካል፣ የፅዳት ዘመቻና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስራዎችን ወጥነት ባለው መልኩ ማከናወን መቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህም ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ከንቲባዋ አንስተዋል።

ለአብነትም በከተማዋ ያሉ ወንዞችን ከብክለት በመከላከልና በመጠበቅ ረገድ ስር ነቀል ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በ44 ወንዞች ላይ የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ወንዞች የብክለት መንስኤ ሳይሆኑ የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ አካል የሆኑ መፀዳጃ ቤቶች ግንባታ፣ የዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ጣቢያዎች፣ የህዝብ መዝናኛ ፓርኮችና የህፃናት መዝናኛና መጫወቻ ስፍራዎችን በአጭር ጊዜ ገንብቶ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

እነዚህንና መሠል ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር ሁለተኛው ዙር ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በቀጣይም ከተማዋን የሚመጥኑና የነዋሪዎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም