በድሬዳዋ የጎርፍ አደጋን ቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ የጎርፍ አደጋን ቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል - ባለስልጣኑ

ድሬደዋ፤ ግንቦት 28/2017(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተለያዩ የጎርፍ መከላከያ ሥራዎች መከናወናቸውን የአስተዳደሩ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።
የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በሚከሰት የጎርፍ አደጋ ለችግር ከሚጋለጡ የሀገራችን ክፍሎች ድሬዳዋ አንዷ ናት።
የአስተዳደሩ የአካባቢ፣ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን እንደገለጸው፣ ባለፉት ዓመታት በድሬዳዋ በአረንጓዴ አሻራ እና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የተከናወኑ ሥራዎች የጎርፍ አደጋ ስጋትን አስቀርቷል።
በተለይም በሐምሌ ወር 1998 ዓ.ም ከተጎራባች የምስራቅ ሐረርጌ ወረዳዎች በመምጣት ድሬዳዋን ያወደመው የጎርፍ አደጋ እንደሀገር ወደር አይገኝለትም ብለዋል።
የአስተዳደሩ የመንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ግንባታ ጥገናና አስተዳደር ዳይሬክተር ያሲን መሐመድ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ ከ1998ቱ ክስተት በኋላ የተቀናጀ የጎርፍ መከላከል ስራዎች ተሰርተዋል።
በጎርፍ መነሻ እና መከሰቻ ወንዞችና አካባቢዎች ላይ የጎርፍ መከላከያ ግንቦች ተገንብተው አደጋውን መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
ዘንድሮ እና አምና በደቻቱና በጎሮ ወንዞች ላይ ከ548 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ወጪ ወንዙ የተፈጥሮ ፍሰቱን ጠብቆ እንዲጓዝ ያስቻሉ የተለያዩ ልማቶች ተከናውነዋል ብለዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በአስተዳደሩ ገጠር ቀበሌዎች የሚከሰትን የጎርፍ አደጋ በመከላከል በኩል ውሃውን ለልማት ማዋል ያስቻሉ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በተለይም ከሁለት ዓመት በፊት በጎርፍ የፈረሰውን ድልድይ በዘመናዊ መንገድ በ137 ሚሊዮን ብር ወጪ መገንባቱ የጎርፍ ስጋትን አስቀርቷል ብለዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ባለስልጣን የደን ልማት ዳይሬክተር ማስረሻ ይመር በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ፣ በተፋሰስ ልማትና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የተከናወኑ ሥራዎች የጎርፍ አደጋን ማስቀረት ችለዋል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት የጎርፍ ምንጭ በሆኑ ተፋሰሶች ላይ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ተጨባጭ ለውጦች ማምጣታቸውን አስረድተዋል።
ዘንድሮም ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ማህበረሰቡን የማንቃት ሥራ እየተሰራ መሆኑን የገለፀው ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ነው።
በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ቡድን መሪ ወንድወሰን በሪ እንዳሉት፤ አደጋን አስቀድሞ ከመከላከል ባሻገር ድንገት ለሚፈጠር ችግር ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል።