የዒድ አል-አድሃ(አረፋ) በዓል ኃይማኖታዊ እሴቱን በመጠበቅ በአብሮነትና የተቸገሩትን በመደገፍ ማክበር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የዒድ አል-አድሃ(አረፋ) በዓል ኃይማኖታዊ እሴቱን በመጠበቅ በአብሮነትና የተቸገሩትን በመደገፍ ማክበር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2017(ኢዜአ)፦ የዒድ አል-አድሃ(አረፋ) በዓል ኃይማኖታዊ እሴቱን በመጠበቅ በአብሮነትና የተቸገሩትን በመደገፍ ማክበር እንደሚገባ የእስልምና ኃይማኖት መምህራን ገለጹ፡፡
1446ኛው የአረፋ በዓል ነገ አርብ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ይከበራል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ትናንት አስተላልፈዋል፡፡
ህዝበ-ሙስሊሙ የዒድ አል አድሃ(አረፋ) በዓልን ሲያከብር በአብሮነትና በመረዳዳት ሊሆን እንደሚገባ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የበዓሉን አከባበርና ኃይማኖታዊ እሴቶች አስመልክቶ የእስልምና ኃይማኖት መምህራን ኡስታዝ በድሩ መሐመድ፣ ኡስታዝ ራህመት ሙዘይን እና ኡስታዝ በድሩ ኑሩ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
በቆይታቸውም የበዓሉ ኃይማኖታዊ ምክንያት ነብዩ ኢብራሂም ፈጣሪያቸውን የመስማትና በፍቅር መታዘዝ የተገለጠበት ነው ብለዋል፡፡
ኡስታዝ በድሩ መሐመድ እንዳሉትም ሕዝበ ሙስሊሙ ዒድ አል-አድሃ(አረፋ)ን ሲያከብር ምስኪኖችንና አቅመ ደካሞችን በማሰብና በማካፈል መሆን እንደሚገባውም ነው የጠቆሙት፡፡
ከኃይማኖታዊ በዓልነቱ በተጨማሪ ያለው ከሌለው ጋር ተካፍሎ የሚውልበት የመረዳዳት በዓል መሆኑን ጠቁመው፤ ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር በአብሮነትና በመረዳዳት ሊሆን እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር ኃይማኖታዊ በዓሉን በመጠበቅ በአብሮነትና የተቸገሩትን በመደገፍ ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ኡስታዝ ራህመት ሙዘይን እና ኡስታዝ በድሩ ኑሩ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ዒድ አል-አድሃ(አረፋ)ን እስላማዊ ሥነ-ሥርዓትንና ሕግጋቱን በመጠበቅና ያላቸውን በማካፈል፣ በዱዓ እና በሌሎች ኃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ማክበር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በዓሉን ሰዳቃን፣ ዱዓን፣ ጾምን፣ ዝክር እና ሰላትን በማብዛት ማክበር እንደሚገባ ጠቁመው፤ በዓሉን በመተሳሰብና በአብሮነት ማሳለፍ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በበዓሉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከዘመድ አዝማድ የሚገናኝበት፣ ከሁሉም ማህበረሰብ ጋር የአብሮነት እሴቶችን የሚያጸናበት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡