የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና አንድነት ከማንኛውም ኃይል መጠበቅ የሚያስችሉ የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት ተገንብተዋል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና አንድነት ከማንኛውም ኃይል መጠበቅ የሚያስችሉ የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት ተገንብተዋል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና አንድነት በተሟላ ሁኔታ ከማንኛውም ኃይል መጠበቅ የሚያስችሉ የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት ተገንብተዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ፈተና እና ስጋት በሰው ውስጥ ያለን እምቅ አቅም ተጠቅሞ ውጤት ማምጣት የሚያስችሉ ጉዳዮች መሆናቸውን አመልክተዋል።
በጸጥታ እና በደህንነቱ ዘርፍ በርካታ ፈተናዎች እንደነበሩ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት በወሰዳቸው እርምጃዎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በሪፎርሙ አማካኝነት ከለውጡ በፊት ከነበረው ሁኔታ ሊወዳደር የማይችል የጸጥታ እና የደህንነት ዘርፍ አቅም መገንባቱን አንስተዋል።
በጸጥታው ዘርፍ ኢትዮጵያ የትኛውን ችግር እና ስጋት በብቃት ማለፍ የሚያስችላት ጠንካራ ቁመና ላይ እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ከደህንነት አኳያም የሳይበር ጥቃቶች በብቃት መመከት እና አስቀድሞ ማምከን የሚያስችል አቅም መፈጠሩንም ነው ያነሱት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሉዓላዊነታችንን በተማሏ ሁኔታ ከማንም ኃይል መጠበቅ እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል።
ጦርነት፣ አንበጣ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ሌሎች ችግሮች ይዘው የመጧቸውን እድሎች ወደ መልካም እድል በመቀየር ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል።
በኮቪድ-ወረርሽኝ ወቅት መሬት ጾም ማደር የለበትም በሚል እሳቤ በዓመት ከሁለት እና ከዚያ በላይ ጊዜ የማምረት ባህልን ለመፍጠር የተደረጉ ጥረቶች ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ወረርሽኙ የፈጠረው የጉዞ ገደብ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈተና እንደነበር አውስተው ይህን አስቸጋሪ ወቅት አውሮፕላኖችን ለእቃ ጭነት (ካርጎ) በማዋል የተከናወነው ስራ አየር መንገዱን ያለ መንግስት ድጋፍ ችግሩን እንዲያልፍ ማድረጉንም አንስተዋል።
መንግስት ከፈተናዎች ውስጥ እድልን ፈልቅቆ በማውጣት እና በመጠቀም ያከናወናቸው ስራዎችም ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።