የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ብክለትን በመከላከል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መስጠት በሚያስችል መልኩ እየተገነቡ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦ የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ብክለትን በመከላከል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መስጠት በሚያስችል ሁኔታ እየተገነቡ መሆኑን የኢፌዴሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ገለጹ።

ነገ ግንቦት 28/2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለ32ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ52ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የአካባቢ ቀን ተከትሎ 2ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ይካሄዳል።


 

ለስድስት ወራት በሚቆየው 2ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄም ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራን ጨምሮ በሕግ ተከባሪነት ውጤት ላስመዘገቡ ተቋማትና ግለሰቦች እውቅና እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ቀኑን አስምልክቶም የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች የአዲስ አባባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶችን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።


 

በዚሁ ወቅት የኢፌዴሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሜ(ኢ/ር)፤ በአዲስ አበባ በወንዝ ዳርቻ ልማት እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች መዲናዋን ጽዱ በማድረግ ውብ ገጽታ እያላበሷት ነው ብለዋል።

በጉብኝቱም በእንጦጦ ፓርክ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት የሚሳተፉ የኮንሶ የአፈር እቀባና እርከን ስራ ሙያተኞች ሀገር በቀል ዕውቀትን የገለጠ ስኬታማ ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ከእንጦጦ ተራራ ጀምሮ የሚገነባው የወንዝ ዳርቻ የአፈር እቀባና የእርከን ስራ ፕሮጀክት የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን በመቀነስ በታችኛው ተፋሰስ ላይ ምቹ የግብርና ልማት ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች የአካባቢ ደኅንነትን በመጠበቅ ለዜጎች ምቹ የኑሮ ምኅዳር እየፈጠረላቸው እንደሚገኝ አንስተዋል።

የከተሞች የኮሪደርና የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራዎችም የአካባቢን ጽዳትና ውብት በማጎናጸፍ ለአካባቢ ጥበቃ ስራ አዎንታዊ ሚና እየተወጡ መሆኑን አስረድተዋል።

የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶችም ብክለትን በመከላከል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መስጠት በሚያስችል መልኩ እየተገነቡ እንደሚገኙ አብራርተዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲዳ ድሪባ፤ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ ጉልህ ፋይዳ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች አፈርና ውሃን በመጠበቅ የመዲናዋን ነዋሪዎች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት እየቀረፉ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በቀጣይም የመዲናዋን ወንዞች ከብክለት በመጠበቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው አገልግሎቶች እንዲሰጡ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ኃላፊ ግዛተ ጊጄ፤ የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢ ደህንነትን በመጠበቅ ትምህርት የሚወሰድባቸው ናቸው ብለዋል።


 

የጋምቤላ ክልል የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ቻንግ ዑቦንግ፤ የመዲናዋ የወንዝ ዳርቻ ልማት ሀገር በቀል ዕፅዋቶችን የሚጠብቅ አስደናቂ ስራዎች መሆናቸውን እንደተገነዘቡ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም