ኢትዮጵያ እና ስሎቪኒያ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ስሎቪኒያ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ስሎቪኒያ የሁለትዮሽ እና የባለብሁ ትብብርን ለማሳደግና ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ።
ኢትዮጵያ እና ስሎቪኒያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት 3ኛውን የፖለቲካ ምክክር መድረክ አካሂደዋል።
በምክክር መድረኩ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ እና ከስሎቪኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ማርኮ ሹትሲን ተወያይተዋል።
አምባሳደር ሀደራ አበራ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ በኢትዮጵያና በስሎቪኒያ መካከል ያለውን ሰፊ የትብብር አቅም አንስተዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማሳደግ፣ አዳዲስ ትብብር መስኮችን ለመለየት እና በሀገሮቹ መካከል ንግድና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን ለመንደፍ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።
የዛሬው ውይይት አሁን ያለውን ትብብርና ተሳትፎ የሚገመግም መሆኑን አመልክተው፤ አዳዲስ የኢኮኖሚ ትብብር መንገዶችን እንደሚፈትሽም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፈጣን አረንጓዴና ዘላቂ የልማት እድገት እያስመዘገበች መሆኑንም ተናግረዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በከፍተኛ ደረጃ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንደከፈተ አምባሳደር ሀደራ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ስሎቪኒያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የጋራ እይታ እንዳላቸው ጠቁመው፤ ሀገራቱ ትብብርን በማጠናከር ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስጠበቅ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የስሎቪኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ማርኮ ሹቲሲን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እና ስሎቪኒያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጋራ ቃል ኪዳኖች እና ግቦች ያላቸው ሁለት ወዳጅ ሀገሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ጠቃሚ አጋር መሆኗን አንስተዋል።
የስሎቪኒያ በቅርቡ በአዲስ አበባ ኤምባሲ መክፈት ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋርም ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎን ለማሳደግ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡፡
የሀገራቸው ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝት በተለያዩ ዘርፎች ማለትም ኢንቨስትመንትና ንግድን ጨምሮ የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የስሎቪኒያ ፕሬዚዳንት ማዳም ናታሳ ፒርክ ሙሳር ለኦፊሴሊያዊ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ እንደሚደርሱም ታውቋል።