ኢትዮጵያዊነት የጋራ እጣ ፈንታ እና ከግል መሻት የተሻገረ ማንነት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊነት የጋራ እጣ ፈንታ እና ከግል መሻት የተሻገረ ማንነት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያዊነት የጋራ እጣ ፈንታ እና ከግል መሻት የተሻገረ ማንነት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ኢትዮጵያዊነት የጋራ ዕጣ ፈንታ ነው።
እንደ ህዝብ የምንደርስበትን ግብና መሻት ልናሳካ የምንችለው በዚህ ትልቅ ማንነት ስር ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ኢትዮጵያዊነት ከትናንት እስከ ዛሬ፣ ከዛሬ እስከ ነገ ማዕቀፍ እንጂ ሲመችና ሳይመች የሚለዋወጥ ማንነት እንዳልሆነም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊነት የማይቆም፣ የነበረ፣ ያለና የሚኖር እንደ ጅረት የሚፈስ ማንነት መሆኑንም እንዲሁ።
ኢትዮጵያዊነት የብሄራዊ ጥቅም አካል መሆኑን በመጠቆም፤ ብሔራዊ ጥቅም ማሳካትና ማበልጸግ የሚቻለው ብሄራዊ ትርክት መገንባትና ትውልድ መስራት ሲቻል እንደሆነም ጠቁመዋል።
ብሔራዊ ጥቅም ከግል ፍላጎትና መሻት የተሻገረ መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያዊነት ማንነት ለሌሎች ማንነት ሁሉ ስር መሆኑን አብራርተዋል።
ሁሉም ማንነቶች በኢትዮጵያዊነት ማንነት ስር የሚወድቁ ናቸውም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ሀገር የቅብብሎሽ ውጤት በመሆኑ ትልውድ እያሰቡ መስራት እንደሚጠይቅ አንስተዋል።
ሀገር ለመገንባት ደግሞ ትናንትን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ በማስተሳሰር እየሰራን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ይህም ከንግግር ባለፈ በተግባር እየተገለጠ መሆኑን በማንሳት ትናንትን የሚዘክሩ ታሪካዊ ቅርሶችን በመጠገን ለትውልድ እንዲሸጋገሩ የተከናወኑ ስራዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ትናንትን በመጠገን ብቻም ነገ አይሰራም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዛሬ ክፍተትን በመፍታት የተሻለ ነገ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።