ቀጥታ፡

ህዝበ-ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ(አረፋ) በዓልን ሲያከብር በአብሮነትና በመረዳዳት ሊሆን ይገባል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦ ህዝበ-ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ(አረፋ) በዓልን ሲያከብር በአብሮነትና በመረዳዳት ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ ገለጹ።

1446ኛው የአረፋ በዓል የፊታችን አርብ ግንቦት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በድምቀት ይከበራል።

በዓሉን በማስመልከት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1446ኛው የአረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቁንም ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

አረፋ ከሐይማኖታዊ በዓልነቱ በተጨማሪ ያለው ከሌለው ጋር ተካፍሎ የሚውልበት የመረዳዳት በዓል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር እርስ በእርስ በመረዳዳትና በአብሮነት ሊያሳልፍ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ አክለውም፤ ወጥቶ መግባት፣ ሰርቶ መብላትና ሀይማኖታዊ ስነስርዓቶችን መከወን የሚቻለው ሰላም ሲረጋገጥ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ከመንግስት ጋር በትብብር እና በጋራ መስራት ይገባናል ነው ያሉት በመግለጫቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም