ቀጥታ፡

የመንገድ ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ አስገዳጅ ደረጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው

አዳማ፤ ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦ የመንገድ ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ አስገዳጅ ደረጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገድ ደህንነትና ፈንድ አገልግሎት ገለፀ።

አገልግሎቱ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ የፀደቁ አስገዳጅ ደረጃዎችን ለባለድርሻ አካላት የማስተዋወቅ መድረክ በአዳማ አካሂዷል።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ሙሐመድ ሀሰን አንደገለጹት የመንገድ ደህንነትን በማረጋገጥ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የትራፊክ አደጋ መፍትሔ ለማበጀት የህግ ማዕቀፎች እየተዘረጉ ናቸው።

ይህም የተሽከርካሪዎች ጥራት፣ የቴክኒክ፣ የመለዋወጫ፣ የቦሎና የደህንነት ቀበቶ አስገዳጅ መስፈርት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ለተግባራዊነቱም ከጉሙሩክ፣ ከባንኮች፣ ከፖሊስ፣ ከትራንስፖርትና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ትብብሩን ለማጠናከር ያለመ ምክክር ማድረጉን አመላክተዋል።

እነዚህ አሰራሮችና የህግ ማዕቀፎች ውጤታማ እንዲሆኑ የባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰው መድረኩ የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ የፀደቁ አስገዳጅ ደረጃዎችን ውጤታማ ለማድረግ የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማሳደግ ነው ብለዋል።

በዚህም በዘርፉ የወጡ ህጎችና አሰራሮች ተፈፃሚ እንዲሆኑና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን ማሳደግ አለባቸው ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የደረጃ ዝግጅት መሪ ስራ አስፈፃሚ ይልማ መንግሥቱ በበኩላቸው የመንገድ ደህንነትና የትራፊክ ፍሰትን ለማረጋገጥ ተሽከርካሪዎች በመንገድ ደህንነት ላይ የፀደቁ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አስገዳጅ ደረጃዎችን ማሟላት አለባቸው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር፣ ከአገልግሎቱና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ተሽከርካሪዎች ዘመኑን የሚመጥን ቴክኖሎጂ በተለይ የፍጥነት መቆጣጠሪያና ገደብ፣ ቴክኒካል ብቃት፣ ቦሎ፣ የተሽከርካሪ መብራትና ፍሬቻዎች፣ የአልኮል መለኪያና የአሽከርካሪዎች ሙያዊ ብቃት እንዲሁም የመንገድ ደህንነት ማረጋገጫ ቁሳቁሶች መሟላት እንደሚገባቸው በህጉ መቀመጡን ጠቅሰዋል።

በመድረኩ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም