በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብርና እገዛ ጥሩ ጅምር የታየበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብርና እገዛ ጥሩ ጅምር የታየበት ነው
ባህር ዳር፤ ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦ በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብርና እገዛ ጥሩ ጅምር የታየበት መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በክልሉ ከሚንቀሳቀሰ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በክልሉ ወቅታዊ የሰላምና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር)፤ በክልሉ ህግን ከማስከበር ጎን ለጎን የልማትና የሰላም ግንባታ ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብርና እገዛ ጥሩ ጅምር የታየበት መሆኑን አንስተው፤ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በመሆኑም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሁሉም አካባቢዎች እየሰፈነ ያለውን ሰላም በማፅናትና ልማትን በማስቀጠል የበኩላቸውን መወጣታቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በሀገር ብሄራዊ ጥቅም፣ በልማትና የህዝብ ተጠቃሚነት ጉዳይ ያለ ልዩነት በጋራ መቆም እንደሚገባ አንስተው፤ በዚህ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎች ይበልጥ ተቀራርበን መስራት አለብን ብለዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ሊቀ መንበር ተስፋሁን አለምነህ፤ ብልጽግና ፓርቲ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ አካታችና ሁሉንም ማዕከል ያደረገ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።
የፖለቲካ ምህዳሩን በመጠቀምም ተፎካካሪዎች በሀገራዊ ጉዳዮች፣ በልማት፣ በሰላምና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም እንዲህ አይነት መልካም ጅምሮችን በማጠናከር የክልሉን ሰላም ዘላቂ ማድረግና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ዳር ማድረስ የጋራ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በኮሪደር ልማት፣ በህዳሴው ግድብ፣ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውና ሌሎች የልማት ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችን አድንቀው፤ በሌሎች መስኮችም ስኬቶችን ለማምጣት በጋራ እንቆማለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
በውይይት መድረኩ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ተሳትፈዋል።