ዲጂታል የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል - ተገልጋዮች

አዲስ አበባ፤ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦ዲጂታል የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ተገልጋዮች ገለጹ።

የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ በቴክኖሎጂ የታገዘ ፍትሃዊ፣ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት መሰጠቱ የዜጎችን የመረጃ ባለቤትነት አረጋግጧል ሲል አስታውቋል።

አዲስ የነዋሪነት መታወቂያ ማውጣትና ማደስ፣የልደት፣የሞት፣ የጋብቻና ጉዲፈቻ ሰርተፍኬት ማግኘት በሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ዲጂታል የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎትን በሚመለከት ኢዜአ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 16 በመገኘት አገልግሎት አሰጣጡን ቃኝቷል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ የጋብቻ ስነ-ስርዓታቸውን ሲፈጽሙ ያገኘናቸው አቶ እያሱ ዋልተንጉስ እና ወይዘሮ ሰላማዊት አክሊሉ የጋብቻ ምስክር ወረቀት ለማግኘት የተሰጣቸው አገልግሎት ቀልጣፋና ዘመናዊ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ እያሱ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት፥ በወረዳው ያለው የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ዲጂታላይዝ መደረጉ ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ገልጿል።

አቶ ሔኖክ ከፍያለውና ወጣት ከተማ አዲስአለም በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል የሲቪል ምዝገባና ወሳኝ ኩነት አገልግሎቶች የተንዛዙና ለብልሹ አሰራር የተጋለጡ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህም ተገልጋዩን ለእንግልትና ለመልካም አስተዳደር ችግር ዳርጎት እንደነበር ገልጸው፥ ተግባራዊ የተደረገው የዲጂታል አሰራር ችግሩን በማቃለል ጥራት ያለው አገልግሎት እንድናገኝ አግዞናል ብለዋል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 16 መሰል አገልግሎቶችን ያገኙ ተገልጋዮችም በወረዳው የሚሰጠው የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት መሻሻሉን ጠቅሰዋል።

የልጃቸውን የልደት ካርድ ለማውጣት የመጡት አቶ መለሰ አበራ እንደገለጹት፥ በወረዳው በተለያዩ ወቅቶች በርካታ አገልግሎቶችን ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

ጽህፈት ቤቱ ቀደም ሲል የነበረበት ቦታ ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ካለመሆኑ ባሻገር የነበረው አሰራር እምብዛም መሆኑን ያስታውሳሉ።

ወይዘሮ የሺወርቅ ግርማ በበኩላቸው፥ ቀደም ሲል ቀናትንና ወራትን የሚፈጁ አገልግሎቶች በአንድ ቀን መጠናቀቅ መጀመራቸው በአሰራሩ ላይ ትልቅ መሻሻል እንደተደረገበት ያሳያል ብለዋል።

ተገልጋዮቹ እንደገለጹት ወረዳው በአሁኑ ወቅት ከተቋም ግንባታ ጀምሮ አሰራሩን ዲጂታላይዝ ማድረጉ ፍትሃዊና ተአማኒ አገልግሎት ለመስጠት አስችሎታል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ እንደገለጹት፥ ተቋሙ አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ያካሔደው ሪፎርም ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል።

ሪፎርሙ በዋናነት በዘርፉ የነበረውን ብልሹ አሰራር መቅረፍ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣን አሰራርን ማስረጽና ምቹ ከባቢያዊ የስራ ሁኔታን መፍጠር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል።

ኤጀንሲው በከተማዋ በ12 ቱም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 119 ወረዳዎች አገልግሎቶቹን በዲጂታል ቴክኖሎጂ አስደግፎ ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቀዋል።

አሰራሩ ቀደም ሲል በተቋሙ ይታይ የነበረውን ህገ-ወጥ አሰራር፣ የሃሰተኛ ሰነድ ዝግጅትና ስርጭትን ለመከላከል፣ለመቆጣጠርና ተጠያቂነትን ለማስፈን ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ነው ያሉት።

በተቋሙ የአገልግሎት ክፍያን ጨምሮ ሁሉም አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ በመደረጋቸው የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ ከማዘመን ባሻገር ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሒደት ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛልም ብለዋል።

ዲጂታል የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት የአሠራር ሥርዓት በተቋሙና በነዋሪዎች መካከል ግልጽ አሰራር እንዲዘረጋ በማስቻል የመረጃ ባለቤትነት እንዲረጋገጥ ማስቻሉን ዋና ዳይሬክተሩ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም