ቀጥታ፡

ተቋሙ ከመደበኛው ተልዕኮው በተጓዳኝ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ነው

ጅማ፤ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ከመደበኛው ሀገራዊ ተልዕኮው በተጓዳኝ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ አገልግሎት በጅማ ከተማ በማህበራዊ አገልግሎት ስራ ያደሳቸውን የአቅመ ደካማ ዜጎች መኖሪያ ቤቶችን አስረክቧል።

የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ተቋሙ ከመደበኛ ሀገራዊ ተልእኮው ባሻገር በመላው ሀገሪቱ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ነው።

በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች በትምህርት ቤቶች ግንባታ፣የመጠጥ ውኃን ተደራሽ በማድረግ እንዲሁም የአቅመ ደካማ ዜጎችን ቤቶች በመገንባት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ተቋሙ ማህበራዊ ሀላፊነቱን መወጣቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፥ በተለይም ሰው ተኮር የሆኑ ሰብዓዊ ስራዎች በትኩረት ይከናወናሉ ብለዋል።

በዛሬው እለትም በጅማ ከተማ በዘጠኝ ሚሊዮን ብር እድሳት የተደረገላቸውና የርክክብ ሥነ ሥርዓት የተከናወነላቸው የአራት አባ ወራዎች መኖሪያ ቤቶችም የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

በጅማ ከተማ ከመኖሪያ ቤቶች ግንባታና እድሳት በተጨማሪ የመዋዕለ ህጻናት ትምህርት ቤትም እየተገየባ መሆኑ ተገልጿል።

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በከተማው እየተወጣ ባለው ማህብራዊ ሀላፊነት አመስግነዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ገልጸው፥ ሌሎች ተቋማትም በመሰል በጎ ስራዎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ቤት ከታደሰላቸው የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ መሀመድአወል አባገሮ፤ቤቴን ለማደስ አቅም አጥቼ በተጨነኩበት ወቅት ቤቴን ስለሰሩልኝ አመሰግናለሁ ብለዋል።

ሌላዋ ቤት የታደሰላቸው ወ/ሮ አባይነሽ መሀመድ፤ ቤታቸው አርጅቶ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው፥ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም