በመዲናዋ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ እውን የሚያደርጉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ እውን የሚያደርጉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፤ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦በመዲናዋ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ እውን የሚያደርጉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ባለስልጣኑ በከተማው የአካባቢ፣የአየርና የወንዞችን ብክለት መከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማ ደረጃ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ እውን የሚያደርጉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር ከባቢን ለመፍጠርም የስነ-ህይወታዊና የስነ-አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ ለአረንጓዴ ልማት የተለዩ አካባቢዎች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ እየተደረጉ ያሉ ስራዎችም ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን መቀነስ የሚያስችሉ አማራጭ ኢነርጂዎች እንዲስፋፉ ቢሮው በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የወንዞች ብክለትን በመከላከል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻልም የወንዝ ዳርቻ ልማት በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ከእንጦጦ ተራራ እስከ ፒኮክ 42 ኪሎ-ሜትር ስፍራዎች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ይህም የወንዞችና የአካባቢ ብክለትን ከመከላከል ባለፈ ዜጎች በፅዱና ምቹ አካባቢ እንዲኖሩ የማስቻል ተግባር ነው ብለዋል።
በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች መበራከታቸው ብሎም ህብረተሰቡ ለአረንጓዴ አሻራ የሰጠው ትኩረት በከተማዋ ብክለትን ለመቀነስ ትልቅ ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአማሔ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ማምረቻ ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ አየለ፥ ማህበራቸው የአየር ብክለትንና የደን መጨፍጨፍን የሚያስቀሩ ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችና ምጣዶች በማምረት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ታየች ወልደስንበት እና የለሚ ኩራ ከፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መሳይ ተክሌ በቤታቸው ማገዶ ቆጣቢ ምድጃና ምጣድ እየተጠቀሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህም ኢትዮጵያ የጀመረችው አረንጓዴ ኢኮኖሚ እውን የሚያደርግና ጊዜ ቆጣቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡