ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች የፍትህ ተደራሽነትን በማረጋገጥ እና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ሚናቸው ከፍተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች የፍትህ ተደራሽነትን በማረጋገጥ እና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ሚናቸው ከፍተኛ ነው
አዲስ አበባ፤ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ማህበራዊ አንድነትን በማስጠበቅ፣የፍትህ ተደራሽነትን በማረጋገጥ እና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የፍትህ ሚኒስቴር እና የሰላም ሚኒስቴር ከደህንነት ጥናቶች ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ሀገር በቀል ባህላዊ ፍትህን ለዳኝነት እና የግጭት አፈታት ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት ሥልጠና ለፌዴራል፣ ከሁሉም ክልሎች እና ከከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ የሰላምና የፀጥታ ቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም አቃቤያነ ህጎች፣ ዳኞች እና የሕግ ባለሙያዎች እየተሰጠ ነው።
በሥልጠናው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ለረጅም አመታት የቆየና የዳበረ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ባለቤት ናት።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚረዱ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በመጠቀም ማህበራዊ አንድነትን በማስጠበቅ፣የፍትህ ተደራሽነትን በማረጋገጥ እና አብሮነትን በማጠናከር የጎላ ሚና እንደሚያበረክቱ ጠቅሰዋል።
በዘርፉ የተገኘውን ውጤት በመገንዘብ መደበኛውን የፍትሕ ሥርዓት ሳይተኩ ማጎልበትና ማበረታታት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሥልጠናው አቃቤያነ ህጎች፣ ዳኞች እና የሕግ ባለሙያዎች በባህላዊ የፍትህ መርሆች ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እና ከመደበኛው የፍትህ ስርዓት ጋር ተደጋግፎ የሚሄድበት ሁኔታዎች ላይ በመወያየት የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፥ ባህላዊ የግጭት አፈታትን ለሠላም ግንባታ እና ለዘላቂ ልማት የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ለማጎልበት እየተሰራ ነው።
ሚኒስቴሩ ለሠላም ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶችን አጥንቶ በመለየት በሥራ ላይ እያዋለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዛሬ የሚሰጠው ሥልጠናም እንደሀገር ያሉትን ማህበራዊ እሴቶች በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያስችል ተናግረዋል።