ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ለዜጎች ኑሮ ምቹ የሆኑና ከብክለት የጸዱ አካባቢዎችን እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ግንቦት 26/2017(ኢዜአ)፦ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ለዜጎች ኑሮ ምቹ የሆኑና ከብክለት የጸዱ አካባቢዎችን እየፈጠረ እንደሚገኝ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ገለጹ።

ከግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሔደውን ሁለተኛ ዙር ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ አስመልክቶ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ52ኛ ጊዜ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም የአካባቢ ቀን ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተለያዩ ኹነቶች እንደሚከበር አስታውቀዋል።

በዕለቱ ሁለተኛው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በይፋ እንደሚጀመርም ዋና ዳይሬክተሯ በመግለጫቸው አንስተዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ የመጀመሪያው ዙር ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ውጤታማ ተግባራት የተከናወኑበት እንደነበር አስታውሰዋል።

የመጀመሪያው ዙር ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከብክለት የፀዳች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታን መፍጠሩንም አንስተዋል።

ሁለተኛው ዙር ንቅናቄው በአገር አቀፍ ደረጃ ለስድስት ወራት እንደሚካሄድ ገልጸው፤ በአንደኛው ዙር የተጀመሩ ተግባራትን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ያግዛል ብለዋል።

በንቅናቄው የውሀ ብክለትን መከላከል፣የፅዳት ዘመቻና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስራዎች ወጥ በሆነ መልኩ እንደሚተገበሩ አስታውቀዋል።

የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ለዜጎች ኑሮ ምቹ የሆነና ከብክለት የጸዳ አካባቢያዊ ሥነ-ምህዳር እየተፈጠረ ለመምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል።

ለስድስት ወራት በሚቆየው አገር አቀፍ ንቅናቄ ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውኑበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ጠቁመዋል።

የመጀመሪያው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ እንደ አገር በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን ለማረምና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማዳበር ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አክለዋል።

ለአብነትም በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ አዋጆችና ህጎች እንዲሻሻሉ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት መሆኑን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት የአካባቢ ጥበቃና ደህንነት ጉዳይ እየዳበረና ባህል እየሆነ መጥቷል ብለዋል።

ንቅናቄው “ፅዱ ኢትዮጵያ እስከ ባሕል” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም