የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ ፤የዜጎች ደህንነትና ጤንነትን ለማስጠበቅ ምቹ ምህዳር የሚፈጥር ነው -ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ግንቦት 26/2017(ኢዜአ)፦የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ ፤የዜጎች ደህንነትና ጤንነትን ለማስጠበቅ ምቹ ምህዳር የሚፈጥር መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፤መስኖ፣ቆላማ አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።    

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 33ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በስብሰባው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተወያየ ሲሆን አዋጁን መርምሮ አጽድቋል።


 

በምክር ቤቱ የውሃ ፤ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር) አዋጁን አስመልክቶ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።      

በዚህም አዋጁ በቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ የሕግ ጥሰቶች ካሉ የእርምት እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች የተካተቱበት ነው ብለዋል።  

ከመኖሪያ ቤት 20 ሜትር ርቀት ድረስ ማጽዳት ግዴታ መሆኑ በአዋጁ መደንገጉን ጠቁመዋል፡፡

ለአካባቢ ብክለት የሚዳርጉ እና አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ምርቶች በሥነ ምህዳር ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት መከላከል ሌላው የአዋጁ ዓላማ መሆኑን አብራርተዋል።   

የቆሻሻ አወጋገድን ዘመናዊ እና ሳይንሳዊ ማድረግ አዋጁ ከያዛቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ሰብሳቢው የሚወገደው ቆሻሻ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ማስቻልንም ያካተተ ነው ብለዋል። 

አዋጁ በሁሉም ክልሎች ተፈጻሚ እንደሚሆን አስታውቀው በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ዘላቂነት ያለው የቆሻሻ አያያዝ ሥርዓት ለመዘርጋት አዋጁ መሰረት የሚጥል መሆኑንም አብራርተዋል።   

አዋጁ በሰዎች ደህንነት እና በአካባቢ ደህንነት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በተሻለ መልኩ ለመከላከል ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት። 

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው አዋጁ የዜጎችን ጤናና ደህንነት ለማስጠበቅ ፋይዳው ጉልህ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም በአዋጁ ዙሪያ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው አዋጁ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲተገበር የባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ ትብብር እንደሚጠይቅም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ምክር ቤቱ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ የተወያየ ሲሆን አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1383/2017 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። 

 

   

 

 

 

   

       

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም