መገናኛ ብዙሃን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ የጀመሩትን አዎንታዊ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ የጀመሩትን አዎንታዊ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ግንቦት 26/2017(ኢዜአ)፦መገናኛ ብዙሃን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ የጀመሩትን አዎንታዊ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር እና የኢዜአ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች "የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞና የሚዲያዎች ሚና" በሚል መሪ ሐሳብ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በሀገራዊ የለውጥ ጉዞ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር፣ የተገኙ ስኬቶችን ማወቅ፣ የገጠሙ ተግዳሮቶችን መረዳት ብሎም የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ተወያይቶ መግባባት ላይ መድረስ ከውይይቱ ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል ናቸው፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር እና የኢዜአ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ያመላከቱ ትላልቅ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
በፖለቲካው ዘርፍ ትርክትን የለወጡ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፉ፣ ለዜጎች መብት መከበር በጎ ሚና የተጫወቱ፣ አካታችነትን በተግባር ያረጋገጡ ብሎም የህዝብን ጥያቄዎች አስተሳስሮ መመለስ ያስቻሉ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በኢኮኖሚው ዘርፍም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እንዲሁም በሌሎች ዘርፎችም ሀገርን ከፍ ያደረጉና የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
በከተማ ልማት፣በዲፕሎማሲ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በሰው ተኮር ስራዎች እንዲሁም በሁሉም ዘርፎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን እንደሀገር በተመዘገቡ ስኬቶች ላይ አስተዋጽኦ ከማድረግ ጎን ለጎን መረጃዎች ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ሲወጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍም የጋራ ትርክትን የሚገነቡ፣ መልካም አፈጻጸሞችን ያስተዋወቁ፣ አጀንዳዎችን ያሰረጹ፣ በመንግስትና ህዝብ መካከል የተሻለ መቀራረብን የፈጠሩ፣ የተቋምና የሀገረ-መንግስት ግንባታን ያሳለጡ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን የህዝቦችን አብሮነት፣ አንድነት፣ ወንድማማችነት እና የጋራ ትርክትን የሚገነቡ ስራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አሳስበዋል፡፡
በሀገረ መንግስት ግንባታ ብሎም በልማት ስራዎች እስካሁን የተከናወኑ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ይህንን ዘላቂ ከማድረግ አኳያ መገናኛ ብዙሃን አዎንታዊ ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አካላት በሃላፊነት ስሜት በመሥራት የማህበረሰብን አብሮነት መገንባት የሚያስችላቸው ስራዎች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት ሀሳብም ከለውጡ ወዲህ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡
የዴሞክራሲ ስርዓቱን ከማስፋት፣ በከተማ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ ብሎም በማህበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች አመርቂ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃንም የተሰሩ ስራዎችን ለህዝቡ ተዳራሽ የማድረግ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ወቅት፤ ኢዜአ በተልዕኮ የተሰጡትን የገጽታ ግንባታና ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር ስራውን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በቀጣይም የብሔራዊነት ትርክትን የሚያጎሉ፣ የድህረ እውነት ዘመንን የሚያዋጁ ብሎም የሀገረ-መንግስት ግንባታን የሚያፋጥኑ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር እና የኢዜአ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በሰጡት ማጠቃለያ፤ የሀገረ መንግስት ግንባታ ስራ የሁለም ኢትዮጵያውያን ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ኢዜአ እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ የዜጎችን አብሮነት የሚጠናክሩ፣ ወንድማማችነትን የሚያጎሉ እንዲሁም ዘመናዊ እና ስልጡን ትውልድ ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት የሚያሳኩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡