ቀጥታ፡

በፈጸምነው ቃለ መሃላ መሰረት ሙያዊ ሥነ ምግባርን አክብረን ለህዝባችን የምንሰጠውን አገልግሎት አጠናክረን እንቀጥላለን - የጤና ባለሙያዎች

ቦንጋ፤ ግንቦት 25/2017(ኢዜአ)፦ በፈጸምነው ቃለ መሃላ መሰረት ሙያዊ ሥነ ምግባርን አክብረን ለህዝባችን የምንሰጠውን አገልግሎት አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ተናገሩ።

የጤና ባለሙያዎችና የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች ክልል አቀፍ የማጠቃለያ የውይይት መድረክ "የጤና ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር ዕድገት" በሚል መሪ ሃሳብ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

የውይይት መድረኩ ታዳሚ ሃኪሞች የሙያው ሥነ ምግባር ከምንም በላይ ሰዎችን ማገልገልና ህይወትን መታደግ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በፈጸምነው ቃለ መሃላ መሰረት ሙያዊ ሥነ ምግባርን አክብረን ለህዝባችን የምንሰጠውን አገልግሎት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።


 

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ዶክተር ሱሌማን ከድር፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ለጤናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ለውጦች እየታዩ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ የጤና ባለሙያውን ተጠቃሚ ያደረጉ አሰራሮች ስለመኖራቸውም ገልጸዋል።   

በመሆኑም አጠቃላይ የህክምና ባለሙያዎች ስነ-ምግባርን ባከበረ መልኩ በቅንነትና በታማኝነት ህዝብን የማገልገል ግዴታ አለብን፤ ይህንንም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።


 

ሌላኛው የህክምና ባለሙያ ሽብሩ ሽኩር፤ የምናገለግለው ራሳችንን፣ ቤተሰባችንን ብሎም ህዝባችንን በመሆኑ የሆስፒታሎችን በር የምንዘጋበት ምንም አይነት ምክንያት ሊኖር አይችልም ሲሉ ተናግረዋል።


 

የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፤ በጤናው ዘርፍ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች አበረታች ውጤቶች እያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ጥረቶች በፍፁም ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን አፅኖት ሰጥተዋል።


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)፣ በክልሉ የጤና ባለሙያዎች ሙያዊ ሥነ ምግባርን ጠብቀው እየሰጡት ላለው የጤና አገልግሎት አመስግነው ይህ ህዝብን የማገልገል ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በጤና ባለሙያዎች ከጥቅማ ጥቅምና ከህክምና ግብዓቶች ጋር በተያያዘ የተነሱ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ የሚመለሱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም