የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርበን የምንሰራበት ወቅት ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርበን የምንሰራበት ወቅት ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 25/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት መስራት የሚገባን ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር "ለተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓትና ባህል ግንባታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ ከተማ አቀፍ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት መድረክ አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳሉት፤ መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።
ብልጽግና የላቀ የፖለቲካ ባህል ለማዳበር ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግሥት ካቢኔ ውስጥ ጭምር እንዲካተቱ መደረጉን ጠቅስዋል።
ይህም አዲስ የፖለቲካ ባህል በተጨባጭ እየተገነባ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ በጋራ ጉዳዮች ላይ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
የፖለቲካ ምህዳርን ይበልጥ ለማስፋት በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርበን የምንሰራበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ወቅቱ ለሀገር እድገት የተሻለ ነገር የሚሰራበት በመሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉትን ተሳትፎ ማጠናከር እንዳለባቸውም ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ምህዳሩን የሚያሰፉ ተግባራት በትኩረት መስራቱን ተናግረዋል።
ምክክር እና ንግግር ጠንካራ የመንግስት ስርዓት ለመገንባት ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቅሰው ይህም ፓርቲዎች በጋራ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ እየተደረገ መሆኑን የሚያሳይ ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አዲስ መሐመድ በበኩላቸው፤ አሁን ላይ መንግስትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በልማት ስራዎች ላይ በጋራ የመስራት ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
በየደረጃው ካሉ የመንግስት መዋቅሮች ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ተናግረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በመድረኩ አስተያየታቸውን የሰጡት የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ክፍለማርያም ሙሉጌታ በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የከተማዋን ገፅታ የቀየሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ(ኢዜማ) ተወካይ ብሩክ አየለ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ(አብን) ተወካይ ማሩ ጃኔ በበኩላቸው፤ መንግስት በሀገራዊ ልማት እና በሀገረ መንግስት ግንባታ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።