በከተማው የሚጣሉ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን በአግባቡ በመሰብሰብ ጥቅም እንዲውሉ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው የሚጣሉ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን በአግባቡ በመሰብሰብ ጥቅም እንዲውሉ እየተደረገ ነው

ደብረ ማርቆስ፤ ግንቦት 25/2017(ኢዜአ)፡- በደብረማርቆስ ከተማ የሚጣሉ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን በአግባቡ በመሰብሰብ ለመልሶ ጥቅም እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑ ተመለከተ።
በየቦታው ያለአግባብ በሚጣሉ የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የአካባቢ ብክለት ለመከላከል የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ የከተማው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ "የፕላስቲክ ብክለትን እንግታ" በሚል ሃሳብ የአለም የአካባቢ ቀንን ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ዛሬ የውይይት መድረክ ያካሄደ ሲሆን፤ ከውይይቱ ተሳታፊ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሰርካለም አዝመራው፤ አካባቢን የሚበክሉ ቆሻሻን በአግባቡ ተሰብስቦ እንዲወገድ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በአካባቢያቸው የሚጣሉ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን ሰብስበው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለሚያደርጉ የተደራጁ ማሀበራት እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ይትባረክ ውዱ በበኩሉ፤ አካባቢን የሚበክሉ ቁሳቁሶችን በመሰብሰብ አካባቢያቸውን ጽዱና ውብ ከማድረግ በተጨማሪ የገቢ ምንጭም እያገኘበት መሆኑን ገልጿል።
በየቦታው ያለአግባብ በሚጣሉ የፕላስቲክና ሌሎች ቆሻሻዎች አካባቢን እንዳይበክሉ አስተዳደሩ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ በመሳተፍ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ተናግሯል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ስለሺ ተመስገን፤ በአካባቢያችን የሚጣለው የፕላስቲክ ቆሻሻ በሰውና እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ብለዋል።
በመሆኑም የአካባቢ ቆሻሻን በአግባቡ በመሰብሰብ ለመልሶ ጥቅም እንዲውል በማድረግ አካባቢን ከብክለት ለመከላከል በከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የዛሬው ውይይት ዓላማም የፕላስቲክ ቆሻሻ ለአካባቢ ብክለት ያለውን ተፅዕኖ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ ቆሻሻን ሲያከማቹ በዘርፍ በዘርፍ ለይተው እንዲያከማቹ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ አካባቢ ጥበቃ ፅዳትና ውበት አረንጓዴ ልማት ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ቸርነት አለማየሁ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የፕላስቲክ ቆሻሻ በአፈር፣ በውሃ፣ በአካባቢ ስነውበትና በአየር ላይ ብክለት የሚያስከትል ነው።
ችግሩን ለመግታት በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ የሚሰሩ ማህበራትን በማጠናከር መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።