ቀጥታ፡

ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፤ግንቦት 25/2017(ኢዜአ)፦በመጪው ዓመት ለሚከናወነው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቅድመ ዝግጅትና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ በመግለጫቸው ቦርዱ በ2018 ለሚያካሂደው ሀገራዊ ምርጫ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዚህም የቦርዱን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በማዘጋጀት ስራ ላይ ማዋሉን ጠቅሰው፤ ስትራቴጂክ ዕቅዱ በ6 ዓምዶች የተዋቀረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011ን ለማሻሻል የመነሻ ሃሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

በአዋጁ ማሻሻያ ላይ ከተካተቱት ሃሳቦች መካከልም የእጩዎች ምዝገባ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ ማከናወን ማስቻል የሚሉ እና ሌሎችም መካተታቸውን ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ከ50ሺህ በላይ የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎችን ለመራጮች ምቹ የማድረግ እንዲሁም የማዘጋጀት ስራዎችን መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።

በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የምርጫ አስፈጻሚዎችን የመመልመል ሂደቶች በበይነ መረብ ለማካሄድ ዝግጅት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተለያዩ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቁመው፤ በተለይም አዲስ ለተመዘገቡት ስልጠናዎች እንደተሰጡ አብራርተዋል።

የመራጮች ምዝገባም ፋይዳ መታወቂያን ጨምሮ በቀበሌ እንዲሁም ማንነትን በሚገልጹ መታወቂያዎች ሁሉ እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም