በከተማ አስተዳደሩ ለክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የችግኝ ዝግጅት እየተደረገ ነው

ጅማ፣ግንቦት 25/2017(ኢዜአ):- በጅማ ከተማ አስተዳደር ለክረምቱ ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የሚተከሉ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ችግኞች ተዘጋጅተዋል።

በጅማ ከተማ የከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ መሀመድ ሀሰን እንዳሉት ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ  የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለዛፍና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች ተዘጋጅተዋል።

ባለፉት ዓመታት በመርሃ ግብሩ የተተከሉት ችግኞች የአካባቢን ስነ ምህዳር ከመቀየርና የከተማን ውበት ከመጨመር አንጻር ለመጪው የተከላ መርሃ ግብር መነሳሳትን ፈጥሯል ብለዋል።


 

በዚህ ክረምት ለተከላ ከተዘጋጁ  ችግኞች ውስጥ  የሻይ ቅጠል፣  ለከተማ ውበት የሚሆኑ፣  ፍራፍሬዎች እና  ለእንስሳት መኖ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።

አቶ መሀመድ አክለውም በችግኝ ዝግጅቱ ለምግብነት የሚውሉ በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ሙዝ፣ ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ እና የመሳሰሉ ይገኙበታል ብለዋል።

የችግኝ ዝግጅቱ በአምስት ቀበሌዎች ባሉ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች የተካሄደ ሲሆን ለችግኞቹም እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።


 

በጅሬን ቀበሌ ችግኝ ጣቢያው ችግኝ በመንከባከብ ላይ የተሰማሩት ሮዛ ሀሰን  እንዳሉት  በክረምት ወቅት የሚተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ከሚያገኙት ወርሃዊ ገቢ ባለፈ ለአረንጓዴ አሻራው መርሃ ግብር  የበኩላቸውን እያበረከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጅሬን ቀበሌ አርሶ አደር አቶ ኢብራሂም አብደላ በበኩላቸው በክረምት ወቅት የሚተከሉ ችግኞችን በግላቸው ማፍላታቸውን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም