ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 33ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤  ግንቦት 25/2017 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 33ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

አዳማ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በሊጉ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ያሸነፈው አዳማ ከተማ በ32 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ማሸነፍ አዳማ ከተማ ከሊጉ ላለመውረድ እያደረገ ባለው ፋክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።

ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ በ48 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት 4 የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ምሽት 12 ላይ አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አርባምንጭ ከተማ በ39 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። ኢትዮጵያ ቡና በ55 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ማሸነፍ አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ተከታታይ ድል እንዲያስመዘግብ ያስችለዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ዝቅ ያደርጋል።

የ33ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

ከ33ኛ እስከ 36ኛ ያሉ ጨዋታዎች በዲኤስቲቪ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኙ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም