የአሰላ ከተማን የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ለማዘመን እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአሰላ ከተማን የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ለማዘመን እየተሰራ ነው

አሰላ፤ግንቦት 24/2017(ኢዜአ)፦የአሰላ ከተማን የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በማዘመን ውብና ፅዱ ከተማን ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የከተማው አስተዳደር ገለፀ።
የመገናኛ ብዙሃን ሀላፊዎች እና ባለሙያዎች በአሰላ ከተማ እየተሰራ ያለውን ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ማዕከልን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱላህ ሀሙ እንደገለጹት፥ አስተዳደሩ የከተማዋን የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ለማዘመን በ185 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የማጣሪያ ማዕከል እያስገነባ ነው፡፡
የከተማውን የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ያዘምናል የተባለው ይኸው ማዕከል በስድስት ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ መሆኑንም ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደ ሲሆን በእስካሁኑ ሂደት 60 በመቶ የግንባታ ሥራው መጠናቀቁን ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።
የማዕከሉ የግንባታ ሂደት ሲጠናቀቅ የፍሳሽ ቆሻሻን ከማጣራት በተጓዳኝ የተጣራውን በማከም ለመስኖና ሌሎች ልማቶች ለማዋል እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እሸቱ ሲርኔሳ እንዳሉት፥በክልሉ በመንግስትና ህዝብ መካከል የተሻለ መግባባት ለመፍጠር የተለያዩ ኢኒሼቲቮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶችን ቅንጅታዊ አሰራርን ይበልጥ በማጠናከር የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት በመንግስት የተከናወኑና እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ለህዝቡ ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ከኦሮሚያ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመቀናጀት የተለያዩ የአገሪቱ የመገናኛ ብዙሃንን በማሳተፍ በመጠጥ ውሃና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የተዘጋጀው የሚዲያ ጉዞ(Imala Miidiyaa) የዚሁ ጥረት አካልና ውጤትም የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።
በሻሸመኔ፣ነጌሌ አርሲ፡ ዶዶላ፡ አሳሳ፡ ባሌ ሮቤ እና አሰላ ከተሞች ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የመገናኛ ብዙሃን ሀላፊዎች እና ባለሙያዎች የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እንቅስቃሴ ጉብኝት ተጠናቋል።