በኪነ-ጥበብ ሙያችን አሰባሳቢ ትርክትን ለመገንባትና አንድነትን ለማፅናት እንሰራለን-የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
በኪነ-ጥበብ ሙያችን አሰባሳቢ ትርክትን ለመገንባትና አንድነትን ለማፅናት እንሰራለን-የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች
ሐረር፣ግንቦት 24/2017(ኢዜአ)፦በተሰማሩበት የኪነ ጥበብ ሙያ ገዢ ትርክትን ለመገንባት እና የህዝብን አንድነት ለማጠናከር ተግተው እንደሚሰሩ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሐረሪ ክልል የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተናገሩ።
የሐረሪ ክልል የባህል፣ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር "ሀገርና ጥበብ፤ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት"በሚል መሪ ሃሳብ በቀጣይ ተልዕኳቸው ላይ ዛሬ መክረዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉትና አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ባለሙያዎች እንደተናገሩት፥በሙያቸው በመታገዝ እንደ አገር የተጀመረውን አገራዊ ገዢ ትርክት ለመገንባትና አንድነትን ለማፅናት ተግተው ይሰራሉ።
ከተሳታፊዎቹ መካከል የቲያትር ፀሐፊው ወጣት ፉአድ ሻሙዲን እንደተናገረው፤ ኪነ ጥበብ የህዝብን አንድነትና ትስስር በማፅናት ረገድ ወሳኝ ሚና አላት።
በመሠረቱት የባህል እና የቲያትር ቡድን እያደረጉት ያለው የኪነ-ጥበብ እንቅስቃሴ የዚሁ ማሳያ መሆኑን ገልጿል።
ወጣት ኒያ ሱሌይማን በበኩሏ፥ ኪነ ጥበብና ሀገር፤ አገርና ጥበብ የተሰናሰሉ በመሆናቸው ጥበብ ለሀገር ዕድገትና አንድነት ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፃለች።
ኪነ-ጥበብ አንድነትን ለማፅናት የሚያስችል ኃይል አለው ያሉት ደግሞ የሙዚቃና የቲያትር ባለሙያው አቶ ማሩፍ አብዱላዲ ናቸው።
አቶ ማሩፍ እንዳሉት፤እነዚህን ምቹ መደላድሎች በመጠቀም የጀመሩትን አገራዊ ገዢ ትርክትና አንድነት የማፅናት ስራ ከፍ ለማድረግ ተቀናጅቶ መስራት ይገባል።
የሐረሪ ክልል የባህል፣ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወልዳ አብዶሽ በበኩላቸው፥ በክልሉ በሚካሄዱ ኃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት እንዲሁም ሁነቶች በመጠቀም እንደ ሀገር የተጀመረውን አሰባሳቢና ገዢ ትርክት ለመገንባት በርካታ ስራዎች ቢሰሩም ከሚጠበቀው አንፃር በቂ አይደሉም ብለዋል።
ይህን ክፍተት ለመድፈን እና የተሻለ ስራ ለመስራት ዛሬ ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በጥናታዊ ፅሁፍ ላይ የተካሄደው ውይይትና የተፈጠረው ግንኙነት ወሳኝ አበርክቶ እንደሚኖረውም ገልፀዋል።