በድሬዳዋ ሲካሄድ የቆየው የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ ሲካሄድ የቆየው የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጠናቀቀ
ድሬደዋ፣ግንቦት 24/2017(ኢዜአ)፦በድሬዳዋ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት እና ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የበላይነት ዛሬ ተጠናቀቀ።
ከግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በድሬዳዋ በተካሄደው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከመላው አገሪቱ የተወጣጡ ከ1 ሺህ 190 በላይ ተተኪ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል።
ከ18 ዓመት በታች በተካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በበላይነት ሲያጠናቅቅ፤ ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ ቀጣዩን ደረጃ በመያዝ እንዲሁም ኦሮሚያ ክልል ሶስተኛ በመውጣት አሸናፊ ሆነዋል።
ከ20 ዓመት በታች በተካሄዱት ውድድሮች ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንደኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ መቻል እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከታዮቹን ደረጃዎች በመያዝ አጠናቀዋል።
በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ አትሌቶችም በመጪው ሐምሌ ወር በናይጄሪያ በሚካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አገር ወክለው እንደሚሳተፉም ታውቋል።
በዕለቱም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መሠረት ደፋር፣ የድሬዳዋ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ እና ሌሎች አመራሮች ለውድድሩ አሸናፊዎች ሽልማቶችን አበርክተዋል።