ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ለሌሎች ተምሳሌት የሆኑ ተግባራት እያከናወነች ነው-የአየር ንብረት ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ለሌሎች ተምሳሌት የሆኑ ተግባራት እያከናወነች ነው-የአየር ንብረት ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፤ግንቦት 24 /2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያከናወነች ያለው ተግባር ለሌሎች ተምሳሌት የሚሆን ነው ሲሉ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የኖርዌይና እንግሊዝ ኤምባሲዎች የአየር ንብረት ባለሙያዎች ገለፁ።
በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ምቹና ሳቢ እያደረጋት መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የኖርዌይ ኤምባሲ የአየር ንብረትና ደን አማካሪ ሊቭ ሳይደንስ እንደገለፁት፤ኢትዮጵያና ኖርዌይ ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ በደንና አየር ንብረት ዙሪያ በትብብር እየሰሩ ይገኛሉ።
ኖርዌይ ኢትዮጵያ በደን ልማት ላይ እየሰራች ላለችው ስራ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን አንስተው፥ኢትዮጵያ ከደን ልማት ተጠቃሚ እንድትሆን የካርቦን ሽያጭና ገበያ ላይ በትብብር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የደን ጭፍጨፋን ለመቀነስና የደን ሽፋንን በማሳደግ ለካርበን ልቀት ቅነሳ እያደረገች ያለው አስተዋፅኦ የሚበረታታና አገሪቱ በጠንካራ የፖለቲካ አመራር ስራውን እየመራች መሆኗን የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ኖርዌይና ኢትዮጵያ በትብብር ከሚሰሩት የደን ልማትና መሬት መልሶ ማገገም ስራዎች ጋር የተጣጣመ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል።
ኖርዌይ ከ1990ዎቹ ጀምሮ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዙሪያ ስትሰራ መቆየቷንና በ2024 በአገሪቱ ከተገዙ ተሽከርካሪዎች 90 በመቶዎቹ የኤሌክትሪክ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ኖርዌይ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የረጅም አመት ልምድ ያላት በመሆኗ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ገልፀዋል።
የእንግሊዝ ኤምባሲ የውጭና የጋራ ልማት ፅህፈት ቤት የአየር ንብረትና ተፈጥሮ ሀብት ኃላፊ ኒና ሂሰን (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር እየሰራች ያለችው ተግባር ለሌሎች አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
ባለፉት ጥቂት አመታት የደን ሽፋኗ እየጨመረ መሆኗን ጠቅሰው፤ ይህንንም ጥረት እንግሊዝ እንደምትደግፍ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ላይ እያከናወነች ላለቻቸው ተግባራት ተጨማሪ ፈንድ ማግኘት እንድትችል እየሰራን ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማበራከት እየሰራች ያለችውን ተግባር አድንቀው፤ ይህንኑ የተመለከተ ጥናት እያካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የጥናቱን ውጤት በአፍሪካ የአየር ንብረትና የኢ ሞቢሊቲ ጉባዔ ላይ ለማቅረብ መታቀዱንም ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ በኮሪደር ልማት የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ የእግረኛና የሳይክል መንገድን ጨምሮ የተሰሩ ስራዎች የሚደነቅ መሆኑንም ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።