ቀጥታ፡

በፌደራል ተቋማትና ማህበራት ደረጃ የተካሄደው 14ኛው የአጃንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ስኬታማ ነበር -ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 24 /2017 (ኢዜአ)፦በፌደራል ተቋማትና ማህበራት ደረጃ የተካሄደው 14ኛው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ስኬታማ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

ኮሚሽኑ ለሶስት ቀናት ሲያካሄድ የቆየው የፌዴራልና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ተጠናቋል።

የሂደቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፥ ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም በ11 ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማካሄዱን ተናግረዋል።

14ኛውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በፌዴራል ተቋማትና በማህበራት ደረጃ መካሄዱን ጠቁመው፥ ይህም ስኬታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በፌደራል ተቋማትና ማህበራት የተካሄደው የምክክር ምዕራፍ ከ38 በላይ ተቋማት መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን የተሰበሰቡ ሁሉም አጀንዳዎች ወደ ኮሚሽኑ ቋት መግባታቸውን ጠቁመው፥በአጀንዳዎቹ ላይ በዋናው የምክክር ጉባኤ ጊዜ መግባባት ላይ እንደሚደረስባቸው ገልጸዋል።

በቀጣይ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደት የሚከናወን መሆኑን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በምክክር ሂደቱ ላይ የማሳተፍ ስራም ቀሪ የኮሚሽኑ ሂደት መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ መልኩም እስካሁን በሂደቱ ላይ ያልተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ሌሎች አካላትን ወደ ሂደቱ እንዲመጡ ይሰራልም ብለዋል።

ኮሚሽኑ እስካሁን ያካሄዳቸውን የምክክር ምዕራፍ በስኬት እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም