ሀገር አቀፍ የወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር አቀፍ የወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ፤ግንቦት 24/2017(ኢዜአ)፦በድሬዳዋ ሲካሄድ የቆየው 13ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች እና 4ኛው ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል።
በሻምፒዮናው ላይ በሁለቱም ጾታዎች ከክልሎች፣ ከአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ ከተሞች የተውጣጡ ከ1 ሺህ 190 በላይ ወጣትና ተተኪ አትሌቶች በተለያዩ የአትሌቲክስ ስፖርቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
የውድድሩ አላማ በቀጣይ በናይጄሪያ አቡኩታ በሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም በሚካሄደው የአፍሪካ ከ18 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተተኪ አትሌቶችን መመልመል መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
ሻምፒዮናው ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ለማፍራት ካለው ፋይዳ ባሻገር ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ወጣቶች የእርስ በርስ ትስስርና አንድነታቸውን የማጠናከር ግብ ይዞ ሲካሄድ ቆይቷል።
ከግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው ሻምፒዮን ዛሬ ይጠናቀቃል።
በሻምፒዮናው መዝጊያ በ1500 ሜትር፣ 400 ሜትር መሰናክል፣ ስሉዝ ዝላይ እና ምርኩዝ ዝላይ በሁለቱም ጾታዎች ከ20 እና 18 ዓመት በታች የእድሜ እርከን የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ።
4×100 የዱላ ቅብብል በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም 4×400 ድብልቅ የዱላ ቅብብል ( ወንድ እና ሴት) ሌሎች የሚደረጉ የፍጻሜ ውድድሮች ናቸው።