ኢትዮጵያ እና ህንድ በተለያዩ መስኮች ያላቸው ትብብር ተጠናክሮ ቀጥሏል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ህንድ በተለያዩ መስኮች ያላቸው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሉን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በህንድ የፓርላማ አባል ሱፕሪያ ሱሌ ከተመራው ልዑክ ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።


 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያና ህንድ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው፡፡

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጠናክሮ እየቀጠለ መሆኑን አንስተው የህንድ ፓርላማ ልዑካን ጉብኝትም የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክረዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የህንድ ኢንቨስተሮች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውንም ጨምረው አስታውቀዋል።

ውይይቱን በተመለከተ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደገለጹት የሀገራቱ ግንኙነት ጥልቅ መሰረት ያለውና ታሪካዊ መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል።

ሀገራቱ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ማረጋገጣቸውንም ጠቁመዋል።

በሁሉም መስኮች ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፥ ይህንንም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በጋራ እንደሚሰሩ በውይይቱ መመላከቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም