ቀጥታ፡

የጤና ባለሙያዎች የሥራ ፍቅርን ያስቀደመ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ነው

ሆሳዕና ፤ ግንቦት 23/2017 (ኢዜአ)፡-የሥራ ፍቅርን ያስቀደመ የህክምና አገልግሎት ለህብረተሰቡ በመስጠት ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የጤና ባለሙያዎች ገለፁ፡፡ 

"የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር እድገት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የጤና ባለሙያዎች የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡

የሀላባ ቁሊቶ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ደግሰው ደሳለኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በሆስፒታሉ  የህክምና ሞያዊ ስነ ምግባርን በተከተለ መንገድ  ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየተሰጠ  ይገኛል፡፡


 

የህክምና ሙያ ለህሙማን ፍቅርና እንክብካቤን መስጠት የሚጠይቅ በመሆኑን ይሀንኑ መሰረት ባደረገ መልኩ ለህብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት አጠናክረው መቀጠላቸውን አስረድተዋል ፡፡

በከምባታ ዞን ዶዮገና ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ባለሙያ አየለች ጠና በበኩላቸው፣ በሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት አሰጣጡን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ጤናማና ብቁ ዜጋን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የጤና ባለሙያዎች ሞያዊ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውንና በተለይም ለእናቶችና ህፃናት ጤና  ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የሕክምና ሞያ ፍቅርንና ርህራሄን መሰረት በማድረግ  ለህሙማን አገልግሎት የሚሰጥበት መሆኑንም አክለዋል። 

በክልሉ የጤና አገልግሎትን ለማጠናከር በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ያወሱት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ናቸው፡፡

የጤና ባለሙያዎችም ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት እያገለገሉ እንዳሉ ጠቅሰው አገልግሎቱን ለማዘመን የጤና ተቋማቱን በግብአትና በሰው ሀይል የማደራጀት ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።


 

በሥራ ሂደት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመሙላት በቅንጅት የሚከናወኑ ተግባራት በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የጤና ባለሙያዎችን ያወያዩት የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ ዲላም ኦቶሬ (ዶ/ር) እንደገለፁት በክልሉ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ  አሳታፊ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በክልሉ  ለሚከናወኑ  የልማት ስራዎች ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ረገድ  የጤና ባለሙያዎች አበርክቶ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

 የጤና ባለሞያዎች ለሀገራቸውና ለህዝባቸው በቁርጠኝነት እያሳዩት ያለው ሞያዊ  ትጋት  ፍቅር  እና መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የጤና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም