ሀገርና ህዝብ የሚመካበት ዘመናዊ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተገንብቷል - የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ሀገርና ህዝብ የሚመካበት ዘመናዊ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተገንብቷል - የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2017(ኢዜአ)፦ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ ሀገርና ህዝብ የሚመካበት ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት መገንባቱን የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሯ በመከላከያ ሠራዊት የተከናወኑ ተግባራትን፣ የተገኙ ስኬቶችንና ቀጣይ ተልዕኮዎችን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ስኬታማ ሪፎርም መደረጉን አንስተው፤ ውትድርና ጀግኖች የሚመርጡት ለሀገር ሉዓላዊ አንድነት ዋጋ የሚከፈልበት የተከበረ ሙያ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሥነ-ምግባር የታነጸ ሀገርና ህዝብ የሚመካበት ፕሮፌሽናል የሀገር መከላከያ ሠራዊት መገንባቱንም አንስተዋል።
የዓለም አቀፍ የጦርነት ስልቶች መለወጣቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትንም ዘመናዊ ትጥቅን በማሟላት የሀገርን ተጋላጭነት ማስቀረት የሚችል አስተማማኝ ኃይል ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
አክለውም ሰራዊቱ በህበረ-ብሔራዊ አንድነት የተዋቀረና ለሀገር ሉዓላዊነት ዘብ የቆመ የመጨረሻው ጠንካራ ምሽግ መሆኑን አብራርተዋል።
ባለፉት ዓመታት በነበሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ መልከ ብዙ ግዳጆችን በብቃት በመወጣት በአደረጃጀት፣ በትጥቅ፣ በአስተሳስብና ስልጠና ነጥሮ የወጣ ዘመናዊ ሠራዊት ሆኗል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ላይ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚቃጣ ጥቃትን ከሩቅ የሚያስቀርና የሚመክት የምድር ኃይል፣ የአየር ኃይል፣ የሜካናይዝድ፣ የባሕር ኃይል፣ የልዩ ዘመቻ እና የሳይበር ኃይል መገንባቱንም አንስተዋል።
ሠራዊቱ ህገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ የሚሞክሩ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የሀገርን ሰላምና ደኅንነት ማፅናቱንም ገልጸዋል።
በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሰላም ችግር የሚፈጥሩ የታጠቁ አካላት ላይ እርምጃ በመውሰድና በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን እንዲሰጡ በማድረግ የዜጎችን ሰላም እያስጠበቀ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የጽንፈኞችና የሽብር ቡድኖችን የስጋት አቅም በማክሰም ስኬታማ የህግ ማስከበር ስራ መሰራቱንም ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
ሠራዊቱ ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመተባበር በሰዎች እና በሸቀጦች እንቅስቃሴ ላይ መስተጓጎል በሚፈጥሩ ጥቂት የጥፋት ኃይሎች ላይ ቀጣይነት ያለው እርምጃ በመውሰድ ሰላማዊ የትራንስፖርት ፍሰት እንዲኖር በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለህዝብ ሰላምና ለሀገር ሉዓላዊ አንድነት የህይወት መስዋዕትነት የሚከፍለውን ሰራዊት በማህበራዊ ሚዲያ በሀሰት ስሙን የሚያጠፉ አካላት መኖራቸውን በማንሳት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችው ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞ እንዳይሳካ የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶቿ ከውስጥ ባንዳዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር እየሰሩ መሆኑንም አንስተዋል።
የራሱን ህዝብ በፍርሃት ተሸብቦ እንዲኖር በማድረግ በተቻለ አጋጣሚ ለስደት የሚዳርግ አካል ስለኢትዮጵያ የመናገር ሞራልም ሆነ ድፍረቱ እንደሌለው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላምና ደኅንነት ያለባት ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሯ የመከላከያ ሠራዊቱን ሁሉን አቀፍ የማድረግ አቅም ቀጣይነት ባለው መልኩ የመገንባቱ ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።