የፌደራል ተቋማትና ማህበራት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ አጀንዳቸውን እያቀረቡ ነው - ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
የፌደራል ተቋማትና ማህበራት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ አጀንዳቸውን እያቀረቡ ነው - ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2017(ኢዜአ)፦ የፌደራል ተቋማትና ማህበራት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳቸውን እያቀረቡ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
ትናንት የተጀመረው የፌደራል የተቋማትና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል።
በምክክር ሂደቱ ከ38 ተቋማትና ማህበራት በርካታ ተወካዮች በመሣተፍ ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዓላማ ሀገራዊ መግባባት መፍጠርና የምክክር ባህልን ማዳበር መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህ አኳያ ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎች ህዝቡ እንዲመካከር በማድረግ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ትናንት በተጀመረው የፌደራል የተቋማትና የማህበራት አጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍም ለኮሚሽኑ ቀጣይ የምክክር ስራ ጠቃሚ ግብዓት የተገኘበት መሆኑን አንስተዋል።
የሀገራዊ ምክክሩን ዓላማ ከማሳካት አኳያም ተሳታፊዎች ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት።
በኢትዮጵያ ዘላቂ የሰላም ግንባታን ለማረጋገጥና ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ባህል ለማዳበር መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ሊሰሩ እንደሚገባም ነው ኮሚሽነሩ ያመለከቱት።
ኢትዮጵያውያን ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተባበረ ክንድ እውን ማድረግ እንደቻሉት ሁሉ ለሰላም ግንባታውም መተባበርና አንድነታቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።
ለዚህም ምክክር ቁልፍ ተግባር በመሆኑ ሁሉም ለሀገራዊ ምክክሩ በጎ ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከጥቂት ወራት በኋላ በትግራይ ክልል እና በዳያስፖራ ማህበረሰብ አጀንዳ የማሰባሰብ ስራውን እንደሚቀጥል ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።