በክልሉ የጤና ተቋማትን አቅም በማሳደግ ተገልጋዩን ለማርካት በተከናወኑ ሥራዎች ውጤቶች ተመዝግበዋል-ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የጤና ተቋማትን አቅም በማሳደግ ተገልጋዩን ለማርካት በተከናወኑ ሥራዎች ውጤቶች ተመዝግበዋል-ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ
ሰመራ፤ ግንቦት 23/2017 (ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል የጤና ተቋማትን አቅም በማሳደግና ተደራሽነትን በማስፋት ተገልጋዩን ለማርካት በተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
“የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር ዕድገት” በሚል መሪ ሀሳብ የጤና ባለሙያዎች የውይይት መድረክ ዛሬ በሠመራ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፤ በለውጡ ዓመታት የጤና ተቋማትን አቅም በማሳደግና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ ብዙ ተሰርቷል፤ ውጤቶችም መጥተዋል ብለዋል።
በክልሉ ከመደበኛ የሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ ተንቀሳቃሽ የሕክምና አገልግሎት ስርአት በመዘርጋት በተለይም ለአርብቶ አደሮች የሕክምና አገልግሎት በስፋት ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በቀጣይ የጤና ተቋማትን በማጠናከርና ጥራት ያለው አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ የተቋማትን ተደራሽነት የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በጤና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታሪኩ በላቸው፤ የጤና ተቋማት አገልግሎታቸውን ይበልጥ በማሻሻል የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ማሳካት እንዳለባቸው አንስተዋል።
ለእዚህም የጤና ባለሙያዎች ብቃት፣ የማገልገል ፍላጎትና ተነሳሽነት ወሳኝ መሆኑን ነው የገለጹት።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሁመድ አርሳይታ (ዶ/ር) ለጤናው ዘርፍ መሻሻል በትኩረት መሰራቱን አንስተዋል።
በተለይም ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በክልሉ የጤና ምርምር ኢንስቲትዩት መቋቋሙ የጤና ሥጋቶችን ለማስቀረት ተጨማሪ አቅም ፈጥሯል ብለዋል።
የጤና ጣቢያዎች እና ጤና ኬላዎችን በተሻለ ግብአት መልሶ በማደራጀት እንዲሁም የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽነት በማስፋት በኩልም ውጤት መታየቱን ነው የጠቆሙት።
በውይይቱ ላይ ከተሳተፉ የጤና ባለሞያዎች መካከል በአይሳኢታ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የእናቶችና ህፃናት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር አህሜ መሐሜ የጤናው ሴክተር ተደራሽነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ይሄም በተለይ የእናቶችን የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚነት ማሳደጉን አመልክተዋል።
በክልሉ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ ከአውራ ወረዳ ጤና ፅህፈት ቤት የመጡት ገዶ አህመድ ናቸው።
ለአብነትም እንደ ኦክሲጂንና ኤክስ-ሬይ ባሉ ዘመናዊ መሳሪያዎች ታግዞ የህክምና አገልግሎት መሰጠቱ አገልግሎቱ እየተጠናከር እንዲመጣ ማገዙን ለአብነት አንስተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኀላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን፣ ሌሎች የክልሉ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም ከሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ታድመዋል።