የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ አካል የሆነ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን የመገንባት ስራ ላይ ትኩረት ተደርጓል - ፌዴሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ አካል የሆነ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን የመገንባት ስራ ላይ ትኩረት ተደርጓል - ፌዴሬሽኑ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2017(ኢዜአ)፦ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ ጥረት አካል የሆነ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መገንባት የሚያስችል የታዳጊዎች ፕሮጀክት እየተተገበረ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትየጵያ የአፍሪካን ዋንጫ እ.አ.አ በ2029 ለማስተናገድ እቅድ እንዳላት መግለጻቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያ በይፋ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድርን ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረቧም ይታወቃል።
ጉዳዩን በተመለከተም ኢዜአ ከዝግጅት አንጻር በተለይ ተፎካካሪ ብሄራዊ ቡድን ለመገንባት ምን እየተሰራ እንደሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ጠይቋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ባህሩ ጥላሁን እንደገለጹት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ በርካታ ተግባራትን ማከናወን ጀምሯል።
በተለይ እአአ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ዕቅድ መያዟን ተከትሎ ጠንካራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በማንሳት በተለይ ተፎካካሪ እና ውጤታማ ብሔራዊ ቡድን መገንባት ላይ ትኩረት መደረጉን አስታውቀዋል።
ከአሁኑ ጀምሮ በተለይ ታዳጊዎች ላይ ያተኮረ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችና ፕሮጀክቶች ተግባራዊ መደረግ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ከእነዚህ መካከል "Road to 2029" ፕሮጀክት በሚል ጥሩ አቅም ያላቸውን ታዳጊዎች በመመልመል ወደ ብሔራዊ ካምፕ በማስገባት ውጤታማ የምዘና እና ስልጠና ስራ መጀመሩን ለአብነት አንስተዋል።
እስካሁንም በአዲስ አበባ አርባ ታዳጊዎች በካፍ የልህቀት ማዕከል እንዲገቡ በማድረግ ስልጠና እንዲያገኙ መደረጋቸውንና በቀጣይም በሌሎች ክልሎች ብቁ ታዳጊዎች ተመርጠው ስልጠና ይወስዳሉ ብለዋል።
በዚህ ሂደት ለውድድሩ ብቁ አቅም ያላቸውን ተጫዋቾች የማፍራትና የማዘጋጀት እቅድ መያዙን አስታውቀዋል፡፡
ይህ አካሄድ የዓለም አቀፍ ልምድ መሆኑን በርካታ ሀገራት ተጠቅመውበት ውጤታማ እንዳደረጋቸውም አቶ ባህሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ እንድታዘጋጅ ፌዴሬሽኑ በርካታ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመው ለውጤታማነቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚሰራውን ስራ በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ጥያቄዋ ምላሽ ካገኘ የሀገሪቱን እግር ኳስ ከማነቃቃት በተጨማሪ የሀገርን ገጽታ ለመገንባት ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም አንስተዋል።