ቀጥታ፡

ጤናማና አምራች ዜጋን በመፍጠር ልማትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የጤና ባለሙያዎች ሚና የማይተካ ነው

ሆሳዕና፤ ግንቦት 23/2017(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤናማና አምራች ዜጋን በመፍጠር ልማትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የጤና ባለሙያዎች ሚና የማይተካ መሆኑን የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

"የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር እድገት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የጤና ባለሙያዎች የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡


 

በዚህ ወቅት የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር) እንዳሉት የጤና ባለሙያዎች ለህብረተሰቡ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት በመስጠት እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ ማጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡

ጤናማና አምራች ዜጋን በመፍጠር ልማትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የጤና ባለሙያዎች ሚና የማይተካ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የሕክምና አገልግሎት ከህግ ማዕቀፍ ባለፈ የበጎ ህሊና ውጤት በመሆኑ ባለሙያዎቹ ባላቸው ሙያ ህብረተሰቡን በቅንነት ሊያገለግሉ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው፣ በክልሉ እየተመዘገበ ያለውን ሁሉን አቀፍ ስኬት አጠናክሮ ለማስቀጠል የጤና ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

መንግስት በጤናው መስክ የጀመራቸው የለውጥ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህን ለማጠናከር በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በተቀናጀ መንገድ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የጤና ባለሙያዎች የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅና ሙያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ጥረታቸውን በማጎልበት ጤናማና አምራች ዜጋን የመፍጠር ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ግዛቸው ቶሌራን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ አመራሮችና የጤና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም