የደሴ ሙዚየም ለጉብኝት ክፍት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የደሴ ሙዚየም ለጉብኝት ክፍት ተደረገ
ደሴ ፤ ግንቦት 23/2017(ኢዜአ)፡- የደሴ ሙዚየም ዛሬ ለጉብኝት ክፍት ተደረገ።
ሙዚየሙ ለጎብኝት ክፍት የተደረገው እድሳቱ በከፊል ተጠናቆ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ተመርቆ ነው።
"ፈጣን እና ተለዋዋጭ በሆነ ማኅበረሰብ የሙዚየም ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ የዓለም ሙዚየም ቀን በደሴ ከተማ እየተከበረ ነው።
የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) በመረሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ሙዚየሙ በነበረው ችግር ጉዳት ደርሶበት ነበር።
ከተለያዩ አጋር ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በተከናወነው ስራ ሙዚየሙ ታድሶ ለዛሬ ምርቃት በመብቃት ለሰው ልጅ አመጣጥ ጥናት መለኪያና ማጣቀሻ የሆነችው የሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሪተ አካልን ጨምሮ ሌሎች ቅርሶችም በሙዚየሙ እንዲጎበኙ ማስቻሉን አስታውቀዋል።
ሙዚየሙ የደሴ ከተማና አካባቢውን ባህል፣ ወግና እሴት ለሌሎች ከማስተዋወቅ ባለፈ አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አንሰተዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መቆያ ማሞ በበኩላቸው፤ ጉዳት ደርሶበት የነበረው የደሴ ሙዚየም ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ታድሶ ለጎብኚዎች መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡
ቀጣይ የሙዚየሙን ግቢ በማስዋብና በማሳመር የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን የብሔራዊ ሙዚየም መሪ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አቶ አንዱዓለም ግርማይ፤ በብሄራዊ ሙዚየም የሚገኙ ቅርሶች መምጣታቸው የአካባቢውን ቱሪዝም ለማነቃቃት ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን በፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ጠቁመው ፤ የደሴና አካባቢው ማኅብረሰብ ሉሲን በመጎብኘት ስለ ሃገሩ ሰፊ እውቀት እንዲኖረው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።
በመረሃ ግብሩ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተሞች ልማት ክላስተር አስተባባሪና የከተማና መሰረት ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን መሀመድን(ዶ/ር) እና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።