ቀጥታ፡

በኢንቨስትመንት ዘርፋ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመቅረፍ ክልሉን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ ተችሏል - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2017(ኢዜአ)፦ በኢንቨስትመንት ዘርፋ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመቅረፍ ክልሉን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ መቻሉን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴና አማራጮች ዙሪያ ፎረም እያካሄደ ነው።

በፎረሙ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር)፣ የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አሕመድ እድሪስ እና ባለሃብቶች ተገኝተዋል።


 

ፎረሙ የክልሉን የኢንቨስትመንት አቅም ለማስፋት ያለመ ሲሆን ለሥራ ፈጣሪዎች ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን መፍጠርንም ያለመ እንደሆነ ተጠቅሷል።

በቴክኖሎጂ እና በንግድ ቴክኒኮች የእውቀት ሽግግር ማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተጠቁሟል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ባለፋት አመታት መንግስት ኢኮኖሚውን በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆም በርካታ ተግባራት እያከናወነ ነው።


 

ክልሉን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው፤ የተለያዩ የፖሊሲ እና የስትራቴጂ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በመሠረተ ልማት፣ በሀይል አቅርቦት፣ በፋይናንስና በአገልግሎት አሰጣጥ ያሉ ማነቆዎችን መፍታት መቻሉንም ለአብነት አንስተዋል።

የክልሉን የኢንቨስትመንት መዳረሻነት ይበልጥ ለማሳደገ ከተከናወኑ አበይት ተግባራት መካከል የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቅሰዋል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው እንደሀገር የኢንቨስትመንት አቅምን ለማሳደግ መንግሥት በርካታ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ማድረጉን ገልጸው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ይህም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በኩል ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልልም ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ የወሰዳቸው እርምጃዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እንደሀገር ዘርፋን ለማሳደግ እየተከናወኑ ላሉ ተግባራት ትልቅ አቅም እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም