በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አሶሳ፤ ግንቦት 23/2017(ኢዜአ):-በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ የፌዴራል፣ የክልሎች፣ እና የከተማ አስተዳደሮች የኢንቨስትመንት አስፈጻሚዎች የጋራ የምክክር መድረክ በአሶሳ ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እንደተናገሩት፤ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ መንግስት የተለያዩ አማራጮችን እየተገበረ ነው።
በዘርፉ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ባለሃብቶች እንዲሰማሩ ህጎችን እና አሰራሮችን በማሻሻል የሪፎርም ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ምቹ የሥራ አካባቢ በመፍጠር አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ አልሚ ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አማራጮች በተለያዩ መድረኮች የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ውጤታማ የኢንቨስትመንት ተደራሽነትን ለማስፋት በሁሉም ክልሎች ዘርፉን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት መምራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር በበኩላቸው፤ በክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲጠናከር ከባለሃብቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የሚገኙ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በማልማት ከክልሉ አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጎልብቶ ለማስቀጠል የክልሉ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስተካከል ምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ ናቸው።
መድረኩ በአሶሳ ከተማ መካሄዱ የክልሉን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው መድረክ የፌዴራል፣ የክልሎች፣ እና የከተማ አስተዳደሮች የዘርፉ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።