ኢትዮጵያ ቀጣናውን በታዳሽ ኃይል መሰረተ ልማት በማስተሳሰር አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካት ጉልህ ሚና እያበረከተች ነው - ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ቀጣናውን በታዳሽ ኃይል መሰረተ ልማት በማስተሳሰር አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካት ጉልህ ሚና እያበረከተች ነው - ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ቀጣናውን በታዳሽ ኃይል መሰረት ልማት በማስተሳሰር አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካት ጉልህ ሚና እያበረከተች እንደምትገኝ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ብቻ ለጎረቤት ሀገራት እና ለክሪፕቶ ማይኒንግ ኩባንያዎች ከቀረበው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ220 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህብረት በአጀንዳ 2063 የበለጸገች አህጉር ለመፍጠር ከያዛቸው ውጥኖች አንዱ በፓን አፍሪካ እሳቤ በአፍሪካ ህዳሴ ላይ የተመሰረተ የተቀናጀ አህጉር መፍጠር አንዱ ነው።
እነዚህ እሳቤዎች እውን ከሚሆኑባቸው ተግባራት መካከል ደግሞ የሀገራት ግንኙነትን የሚያሳልጡ መሰረተ ልማት ግንባታ መዘርጋት ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኃይል መሰረተ ልማት በማስተሳሰር የመሪነት ሚናዋን በመወጣት ላይ ትገኛለች።
በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር) ኢትዮጵያ ካሏት በረከቶች አንዱ የውሃ ሀብት መሆኑን ገልጸዋል።
የውሃ ሀብቷን ለታዳሽ ኃይል ልማት ለመጠቀም እየሰራች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ከምታመነጨው የኤሌክትሪክ ታዳሽ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ተደራሽ እያደረገች ነው ብለዋል።
አሁንም ጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ሀገራት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን አንስተው፥ ለኃይል ፍላጎት ጥያቄዎችም በጥናት ላይ የተመሰረተ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኬንያ እና ታንዛኒያ የኃይል ትስስር ለመፍጠር ከኢትዮጵያ የሚሰራጭ የኃይል ምንጭን መሰረት ማድረጋቸውን በማንሳት፥ በቀጣይም እስከ ደቡብ አፍሪካ ኃይል ለማቅረብና አህጉራዊ ትስስርን ለማጠናከር እንሰራለን ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ለሱዳን፣ ለጅቡቲ እና ለኬንያ ለብዙ ዓመታት ኃይል ስታቀርብ መቆየቷን ጠቁመው፥ ከዚህ የምታገኘው ገቢም እያደገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ብቻ ለጎረቤት ሀገራት እና ለክሪፕቶ ማይኒንግ ኩባንያዎች ከቀረበው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ220 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አብራርተዋል።
ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ እድገት አለው ብለዋል።
ኃይል የማመንጨት ሀገራዊ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን በመጥቀስ ይህም ለቀጣናው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ምላሽ የመስጠት ሙሉ ዝግጁነታችንን ያሳያል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት ከጎረቤት ሀገራት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት መኖሩንና ለዚህም ትልቅ አቅም እንዳለ ገልጸው ለአብነትም በዘጠኝ ወራት ውስጥ 6 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መቻሉን አመላክተዋል።
ይህም በጎረቤት ሀገራትና በሁሉም አካባቢዎች ሊሰራጭ የሚችል ኃይል መሆኑን በማንሳት፥ ትልልቅ ኃይል መሸከም የሚችሉ ማስተላለፊያ መስመሮችም ወደ ጎረቤት ሀገራት መዘርጋታቸውን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ በታዳሽ የኃይል ልማት ዘርፍ እያከናወነች ያለው ስራ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ ጉልህ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝም አንስተዋል።
የአካባቢው ሀገራት የአረንጓዴ ኢነርጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ከአካባቢ ብክለት የጸዳ ከባቢን መፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ሀገሪቱ ለጎረቤቶቿ የምታቀርበው የኃይል መሰረተ ልማት ትስስር ገቢ ከማስገኘት ባለፈ የቀጣናውን ህዝብ በጋራ የመልማት ፍላጎት በማሳካት ረገድ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።
ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ የኃይል መሰረተ ልማት ትስስርን በመፍጠር በጋራ ጉዳዮች ላይ ያላትን ተደማጭነት ከፍ ያደርጋል ብለዋል።
እነዚህ ስራዎች በጋራ የመልማት እና ተባብሮ የማደግ እንዲሁም አህጉራዊ ግቦች እውን እንዲሆኑ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል።