ቀጥታ፡

በመዲናዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጡ ናቸው-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብፁዓን አባቶች

አዲስ አበባ፤ግንቦት 22/2017(ኢዜአ)፦በመዲናዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጡ ናቸው ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብፁዓን አባቶች ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ ከለውጡ ወዲህ የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶት ተገንብተው ለህዝብ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል፥ በጉብኝታቸው ማራኪና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ የልማት ስራዎች ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸው የተለየ እንደሚያደርገው ገልጸው፥ የዜጎችን ህይዎትም እጅግ ያሻሻሉና ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡

በጉብኝቱ በልማት የተነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደርን መመልከታቸውን ገልጸው፥ነዋሪዎቹ አሁን ያሉበት አኗኗር ከበፊቱ በብዙ እጥፍ የተሻለ መሆኑን እንደሚያሳይም ገልጸዋል፡፡

በተለይም ተተኪውን ትውልድ በተገቢው ለማነጽ ምቹ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም በመከናወን ላይ ያሉ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ለዚህም የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጋምቤላ ክልል የቄሌም ወለጋ፤የምዕራብ ወለጋ ፤ የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፤ የምስራቅ ወለጋ፤ የአሶሳ እና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል በበኩላቸው፥ በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸውን በተግባር መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም መደሰታቸውን ገልጸው፥በቀጣይ በሚከናወኑ ስራዎችም የበኩላቸውን ለመወጣት ቃል የገቡበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም