ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የላቀ ድርሻ አለው-ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ(ፕ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የላቀ ድርሻ አለው-ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ(ፕ/ር)
ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የላቀ ድርሻ እንዳለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገለጹ።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የፌዴራል የተቋማትና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በምክክር ሂደቱ ከ38 ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች በመሣተፍ ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ የነጻነት ተምሣሌት ፋና ወጊ የበርካታ ቋንቋ፣ ባህል እና እሴት ሀገር ናት ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክር የሃሳብ ልዩነቶችን ተቀራርቦ በውይይት መፍታት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በምክክር ሂደቱ አለመግባባቶችን በውይይት የሚፈቱበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ዛሬ በፌዴራል ተቋማትና ማህበራት ደረጃ እያካሄደ የሚገኘው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ 14ኛ መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደትን ማካሄድ እንዲሁም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ እንደሚቀሩትም ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ወደ ዋናው የምክክር ሂደት ለመግባት የመዳረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በጉዞው አካታችነት እና አሳታፊነትን ተግባራዊ ሲያደርግ መምጣቱንም ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የላቀ ድርሻ እንዳለውም ገልጸዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ስር የሰደዱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጉልህ ሚና ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ኮሚሽኑ እስካሁን ባደረጋቸው የምክክር መድረኮች በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በፌደራል ደረጃ የተለያዩ የተሳታፊ ልየታ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የተለያዩ አጀንዳዎችን መሰብሰቡን ጠቁመው፥በአሁኑ ጊዜ 1ሺህ 234 ወረዳዎች በህዝባዊ ውይይት ወኪሎችን መለየታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ዛሬ የተጀመረው የምክክር ምዕራፍ እስከ ግንቦት 24 ቀን 2017 የሚካሄድ ይሆናል።