ኢንስቲትዩቱ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል ውጤታማ ምርምሮችን ይፋ እያደረገ ነው -ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል ውጤታማ ምርምሮችን ይፋ እያደረገ ነው -ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 22/2017(ኢዜአ)፦አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል የተለያዩ ውጤታማ ምርምሮችን ይፋ እያደረገ እንደሚገኝ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ገለጹ።
የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ኢንስቲትዩቱ ለተለያዩ በሽታዎች መፍትሔ የሚሆኑ ምርምሮችን በትኩረት እያከናወነ ይገኛል።
ባለፉት አመታት ያከናወናቸው የምርምር ተግባራት ለተለያዩ ህክምናዎች የሚያገለግሉ ውጤታማ የምርምር ተግባራትን ማከናወኑን አስታውቀዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የምርምር ተግባራቶቹን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በተለይ መድሃኒቶችና ክትባቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ሂደቱን ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ለመድሃኒት ምርት ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ መተካት የሚያስችሉ ምርምሮች መጀመራቸውን ነው ያብራሩት።
የመድሃኒት ምርት ግብዓትን ለማምረት የተጀመረው ስራ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ የኢትዮጵያ መድሃኒቶች ጥራታቸውንና ደረጃቸውን ጠብቀው በአለምአቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ኢንስቲትዩቱ ቀደም ሲል የአለም ተግዳሮት የሆነው መድሃኒትን ለተላመደ ቲቢ ለማከም የሚወስደውን ጊዜ ከነበረበት 9 ወራት ወደ ስድስት ወራት ዝቅ የሚያደርግ የምርምር ስራ ይፋ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከቲቪ ባለፈ ለማጅራት ገትርና ለኮሌራ መከላከያ የሚሆኑ ክትባቶች ላይ አዲስና ውጤታማ ምርምር በማድረግ መፍትሄ መስጠቱን ተናግረዋል።
እነዚህ የተሻሻሉ ክትባቶች በአለም ጤና ድርጅትና በተለያዩ አለምአቀፍ ተቋማት ዕውቅና የተሰጣቸውና ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት እየተጠቀሙበት መሆኑንም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ለመጣው የወባ በሽታ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖን እንዲሁም የወባ በሽታ አምጪ ተህዋስያን ላይ ምርምሮችን በማድረግ አዳዲስ መፍትሔ ለመስጠት እየሰራ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
በሥጋ ደዌ የጀመረው ምርምር አሁን ላይ አድማሱን አስፍቶ ካንሰርን ጨምሮ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ ምርምሮችን እያደረገ ይገኛል።